ማቴዎስ 21:12-22

ማቴዎስ 21:12-22 NASV

ከዚያም ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚሸጡትንና የሚገዙትን አስወጣቸው፤ የገንዘብ ለዋጮችን ጠረጴዛና የርግብ ሻጮችን መቀመጫ በመገለባበጥ፣ “ ‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ ተጽፏል፤ እናንተ ግን፣ ‘የወንበዴዎች ዋሻ’ አደረጋችሁት” አላቸው። በቤተ መቅደሱም ውስጥ ዐይነ ስውሮችና ሽባዎች ወደ እርሱ ቀረቡ፤ እርሱም ፈወሳቸው። ነገር ግን የካህናት አለቆችና የኦሪት ሕግ መምህራን ያደረጋቸውን ታምራትና፣ “ሆሳዕና፤ ለዳዊት ልጅ” እያሉ በመቅደስ የሚጮኹትን ሕፃናት ባዩ ጊዜ በቍጣ ተሞሉ። እነርሱም፣ “እነዚህ ሕፃናት የሚሉትን ትሰማለህ?” አሉት። ኢየሱስም፣ “አዎን እሰማለሁ፤ እንዲህ የሚለውን ከቶ አላነበባችሁምን? “ ‘ከልጆችና ጡት ከሚጠቡ፣ ሕፃናት አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ።’ ” ትቷቸው ከከተማው ወጣ፤ ወደ ቢታንያም ሄዶ በዚያው ዐደረ። ኢየሱስ በማግስቱም ማለዳ ወደ ከተማዪቱ በመመለስ ላይ ሳለ ተራበ፤ በመንገድ ዳርም አንድ የበለስ ዛፍ አይቶ ወደ እርሷ ሲሄድ ከቅጠል በቀር ምንም ስላላገኘባት፣ “ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ፍሬ አይኑርብሽ!” አላት፤ የበለሷም ዛፍ ወዲያውኑ ደረቀች። ደቀ መዛሙርቱም የሆነውን አይተው በመደነቅ፣ “የበለሷ ዛፍ እንዴት በአንዴ ልትደርቅ ቻለች?” አሉ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ እምነት ቢኖራችሁ ባትጠራጠሩ፣ በበለሷ ዛፍ ላይ የሆነውን ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ይህን ተራራ፣ ‘ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር’ ብትሉት እንኳ ይሆናል፤ አምናችሁም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች