ማቴዎስ 20:1-28

ማቴዎስ 20:1-28 NASV

“መንግሥተ ሰማይ ለወይኑ ቦታ ሠራተኞችን ለመቅጠር ማልዶ የወጣን የአትክልት ስፍራ ባለቤት ትመስላለች። በቀን አንዳንድ ዲናር ሊከፍላቸው ከተስማሙ በኋላ ሠራተኞቹን በወይኑ ቦታ አሰማራቸው። “ከጧቱ ሦስት ሰዓት ላይ በመውጣት ሥራ ፈትተው በገበያ ቦታ የቆሙትን ሌሎች ሰዎች አግኝቶ፣ ‘እናንተም ሄዳችሁ በወይኔ ቦታ ሥሩ፤ ተገቢውን ክፍያ እሰጣችኋለሁ’ አላቸው፤ እነርሱም ሄዱ። “ከቀኑ በስድስት ሰዓትና በዘጠኝ ሰዓት ላይ ወጥቶ ሌሎች የቀን ሠራተኞችን ቀጠረ። ከሰዓት በኋላም በዐሥራ አንድ ሰዓት ገደማ ወጥቶ ቆመው የነበሩ ሌሎች ሰዎች አገኘና፣ ‘ቀኑን ሙሉ ያለ ሥራ እዚህ ለምን ትቆማላችሁ?’ በማለት ጠየቃቸው። “እነርሱም፣ ‘የሚቀጥረን ሰው ስለ ዐጣን ነው’ አሉት። “እርሱም፣ ‘እናንተም ሄዳችሁ በወይኔ ቦታ ሥሩ’ አላቸው። “በመሸም ጊዜ የወይኑ አትክልት ባለቤት የሠራተኞቹን ተቈጣጣሪ፣ ‘ኋላ ከመጡት ጀምረህ መጀመሪያ እስከመጡት ድረስ ያሉትን ሠራተኞች በሙሉ ጥራና ደመወዛቸውን ክፈላቸው’ አለው። “በዐሥራ አንደኛው ሰዓት ገደማ የተቀጠሩት ሠራተኞች ቀርበው፣ እያንዳንዳቸው አንዳንድ ዲናር ተቀበሉ። በመጀመሪያ የተቀጠሩት ሲቀርቡ ብልጫ ያለው ክፍያ የሚያገኙ መስሏቸው ነበር፤ ነገር ግን እነርሱም አንዳንድ ዲናር ተከፈላቸው። ክፍያውን ሲቀበሉ በባለቤቱ ላይ በማጕረምረም፣ ‘እነዚህ በመጨረሻ የተቀጠሩት አንድ ሰዓት ብቻ ሲሠሩ፣ ቀኑን ሙሉ በሥራ ስንደክምና በፀሓይ ስንንቃቃ ከዋልነው ጋራ እንዴት እኩል ትከፍለናለህ?’ አሉት። “እርሱም አንደኛውን ሠራተኛ እንዲህ አለው፤ ‘ወዳጄ ሆይ፤ በደል አላደረስሁብህም፤ በአንድ ዲናር ለመሥራት ከእኔ ጋራ ተስማምተህ አልነበረምን? በል ድርሻህን ይዘህ ሂድ፤ ለአንተ የሰጠሁትን ያህል በመጨረሻ ለመጣውም ሰው መስጠት እፈልጋለሁ። ታዲያ በራሴ ገንዘብ የፈለግሁትን ማድረግ አልችልምን? ወይስ ቸር በመሆኔ ምቀኛነት ያዘህን?’ “ስለዚህ ኋለኞች ፊተኞች፣ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ።” ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ ላይ ሳለ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ለብቻቸው ወስዶ እንዲህ አላቸው፤ “እንግዲህ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፤ የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለጸሐፍት ዐልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም የሞት ፍርድ ይፈርዱበታል፤ እንዲያላግጡበት፣ እንዲገርፉትና እንዲሰቅሉት ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤ በሦስተኛውም ቀን ከሞት ይነሣል።” ከዚያም፣ የዘብዴዎስ ልጆች እናት ከልጆቿ ጋራ ወደ ኢየሱስ ቀርባ በፊቱ ተንበርክካ እየሰገደች፣ አንድ ነገር እንዲያደርግላት ለመነችው። እርሱም፣ “ምን ትፈልጊያለሽ?” አላት። እርሷም፣ “እነዚህ ሁለት ልጆቼ፣ በመንግሥትህ አንዱ በቀኝህ፣ አንዱ በግራህ እንዲቀመጡ ፍቀድ” አለችው። ኢየሱስም መልሶ፣ “የምትለምኑትን አታውቁም፤ እኔ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ ትችላላችሁን?” አላቸው። እነርሱም፣ “እንችላለን” አሉት። እርሱም፣ “ከጽዋዬ በርግጥ ትጠጣላችሁ፤ ነገር ግን በቀኜና በግራዬ መቀመጥ አባቴ ላዘጋጀላቸው ነው እንጂ እኔ የምፈቅደው ነገር አይደለም” አላቸው። ዐሥሩም ይህን በሰሙ ጊዜ፣ ሁለቱን ወንድማማቾች ተቈጧቸው። ኢየሱስ ግን ወደ ራሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “የአሕዛብ ገዦች በሕዝባቸው ላይ ጌቶች እንደሚሆኑ፣ ባለሥልጣኖቻቸውም በእነርሱ ላይ እንደሚሠለጥኑባቸው ታውቃላችሁ፤ በእናንተ መካከል ግን እንዲህ መሆን የለበትም። ከእናንተ ትልቅ መሆን የሚፈልግ አገልጋያችሁ ይሁን፤ ፊተኛ ለመሆን የሚፈልግ ሁሉ፣ የእናንተ ባሪያ ይሁን፤ የሰው ልጅ እንዲያገለግሉት ሳይሆን፣ ለማገልገልና ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ለመስጠት መጥቷልና።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች