ማቴዎስ 19:16-28

ማቴዎስ 19:16-28 NASV

ከዚያም አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፣ “መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ልሥራ” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “ስለ መልካም ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ? መልካም የሆነ አንዱ ብቻ ነው፤ ወደ ሕይወት ለመግባት ከፈለግህ ግን ትእዛዞቹን ጠብቅ” አለው። ሰውየውም፣ “የትኞቹን ትእዛዞች?” ሲል ጠየቀ። ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “አትግደል፣ አታመንዝር፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፤ አባትህንና እናትህን አክብር፤ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።” ጕልማሳውም ሰው፣ “እነዚህንማ ጠብቄአለሁ፤ ከዚህ ሌላ የሚጐድለኝ ምን አለ?” አለው። ኢየሱስም፣ “ፍጹም ለመሆን ከፈለግህ፣ ሄደህ ንብረትህን ሁሉ ሸጠህ ለድኾች ስጥ፤ በሰማይ ሀብት ይኖርሃል፤ ከዚያም መጥተህ ተከተለኝ” አለው። ጕልማሳው ሰውም ይህን ሲሰማ፣ ብዙ ሀብት ስለ ነበረው እየተከዘ ሄደ። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አለ፤ “እውነት እላችኋለሁ፣ ለሀብታም ወደ መንግሥተ ሰማይ መግባት ከባድ ነው። ደግሜ እላችኋለሁ፤ ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀልላል።” ይህን ሲሰሙ፣ ደቀ መዛሙርቱ እጅግ በመገረም፣ “ታዲያ ማን ሊድን ይችላል?” ሲሉ ጠየቁ። ኢየሱስም አያቸውና፣ “ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉም ነገር ይቻላል” አላቸው። ጴጥሮስም መልሶ፣ “እነሆ፤ እኛ ሁሉን ትተን ተከትለንሃል፤ ታዲያ ምን እናገኝ ይሆን?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ በሚመጣው አዲስ ዓለም የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን ላይ በሚቀመጥበት ጊዜ፣ እናንተም የተከተላችሁኝ በዐሥራ ሁለት ዙፋን ላይ ተቀምጣችሁ፣ በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ላይ ትፈርዳላችሁ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች