ማቴዎስ 19:1-22

ማቴዎስ 19:1-22 NASV

ኢየሱስ ይህን ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ፣ ገሊላን ትቶ ከዮርዳኖስ ማዶ ወዳለው ወደ ይሁዳ አውራጃ ሄደ። ብዙ ሕዝብም ተከተለው፤ በዚያም ፈወሳቸው። ፈሪሳውያንም ሊፈትኑት ቀርበው፣ “አንድ ሰው በማንኛውም ምክንያት ሚስቱን እንዲፈታ ተፈቅዷልን?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አድርጎ እንደ ፈጠራቸው አላነበባችሁምን? እንዲህም አለ፤ ‘ስለዚህ፣ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋራ ይጣመራል፣ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’ ከእንግዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው።” እነርሱም፣ “ታዲያ፣ ሙሴ አንድ ወንድ የፍችውን ጽሕፈት ሰጥቶ ሚስቱን እንዲያሰናብት ለምን አዘዘ?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ሙሴ የልባችሁን ጥንካሬ አይቶ ሚስቶቻችሁን እንድትፈቱ ፈቀደላችሁ እንጂ ከመጀመሪያው እንዲህ አልነበረም፤ እላችኋለሁ፤ ዝሙት ፈጽማ እስካልተገኘች ድረስ፣ ሚስቱን ፈትቶ ሌላ ሴት የሚያገባ ሁሉ አመንዝራ ይሆናል፤ እርሷንም አመንዝራ ያደርጋታል፤ የተፈታችውንም ሴት የሚያገባ ያመነዝራል።” ደቀ መዛሙርቱም፣ “የባልና የሚስት ጕዳይ እንዲህ ከሆነ አለማግባት ይሻላል” አሉት። ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፤ “ከተሰጣቸው በቀር ይህን ትምህርት ማንም ሊቀበል አይችልም፤ ምክንያቱም አንዳንዶች ጃንደረባ ሆነው ይወለዳሉ፤ ሌሎች በሰው እጅ ተሰልበው ጃንደረባ ይሆናሉ፤ ደግሞም ለመንግሥተ ሰማይ ሲሉ ራሳቸውን ጃንደረባ የሚያደርጉ አሉ። ይህን መቀበል የሚችል ይቀበል።” ከዚያም እጆቹን በላያቸው ላይ እንዲጭንባቸውና እንዲጸልይላቸው ሕፃናትን ወደ እርሱ አቀረቧቸው። ደቀ መዛሙርቱ ግን ሕፃናቱን ያመጡትን ሰዎች ገሠጿቸው። ኢየሱስም፣ “ሕፃናት ወደ እኔ እንዲመጡ ፍቀዱላቸው፤ አትከልክሏቸውም፤ መንግሥተ ሰማይ እንደ እነዚህ ላሉት ናትና” አላቸው። እጁንም ከጫነባቸው በኋላ ከዚያ ስፍራ ተነሥቶ ሄደ። ከዚያም አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፣ “መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ልሥራ” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “ስለ መልካም ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ? መልካም የሆነ አንዱ ብቻ ነው፤ ወደ ሕይወት ለመግባት ከፈለግህ ግን ትእዛዞቹን ጠብቅ” አለው። ሰውየውም፣ “የትኞቹን ትእዛዞች?” ሲል ጠየቀ። ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “አትግደል፣ አታመንዝር፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፤ አባትህንና እናትህን አክብር፤ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።” ጕልማሳውም ሰው፣ “እነዚህንማ ጠብቄአለሁ፤ ከዚህ ሌላ የሚጐድለኝ ምን አለ?” አለው። ኢየሱስም፣ “ፍጹም ለመሆን ከፈለግህ፣ ሄደህ ንብረትህን ሁሉ ሸጠህ ለድኾች ስጥ፤ በሰማይ ሀብት ይኖርሃል፤ ከዚያም መጥተህ ተከተለኝ” አለው። ጕልማሳው ሰውም ይህን ሲሰማ፣ ብዙ ሀብት ስለ ነበረው እየተከዘ ሄደ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች