ማቴዎስ 18:21-34

ማቴዎስ 18:21-34 NASV

በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፣ “ጌታ ሆይ፤ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? እስከ ሰባት ጊዜ ነውን?” አለው። ኢየሱስም “እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ ብቻ አልልህም” አለው። “ስለዚህ መንግሥተ ሰማይ፣ በባሪያዎቹ እጅ የነበረውን ሒሳብ ለመተሳሰብ የፈለገን ንጉሥ ትመስላለች። ሒሳቡን ማጣራት እንደ ጀመረም ዐሥር ሺሕ ታላንት ዕዳ ያለበትን አንድ አገልጋይ አቀረቡለት። አገልጋዩም ያለበትን ዕዳ መክፈል ስላቃተው እርሱ ራሱ፣ ሚስቱ፣ ልጆቹና ንብረቱ ሁሉ ተሸጠው ዕዳው እንዲከፈል ጌታው አዘዘ። “በዚህ ጊዜ ባሪያው እግሩ ላይ ወድቆ፣ ‘ታገሠኝ፣ ያለብኝን ዕዳ ሁሉ እከፍልሃለሁ’ ሲል ለመነው። ጌታውም ዐዘነለትና ባሪያውን ማረው፤ ዕዳውንም ትቶለት አሰናበተው። “ያ ባሪያ ከጌታው ፊት እንደ ወጣ አንድ መቶ ዲናር የርሱ ዕዳ ያለበትን አገልጋይ ባልንጀራውን አግኝቶ ዕንቅ አድርጎ በመያዝ፣ ‘ያለብህን ዕዳ ክፈለኝ!’ አለው። “ባልንጀራው አገልጋይም ከፊቱ ወድቆ፣ ‘ታገሠኝ፤ እከፍልሃለሁ’ ብሎ ለመነው። “ነገር ግን ሊታገሠው ፈቃደኛ ስላልነበረ፣ ያለበትን ዕዳ እስኪከፍለው ድረስ ወህኒ ቤት አስገባው። የሆነውን ነገር ያዩ ሌሎች አገልጋዮችም በጣም ዐዘኑ፤ ሄደውም ሁኔታውን በሙሉ ለጌታቸው ነገሩት። “በዚህ ጊዜ ጌታው ባሪያውን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ ‘አንተ ክፉ ባሪያ፤ ስለ ለመንኸኝ ያን ሁሉ ዕዳ ተውሁልህ፤ እኔ እንደ ማርሁህ አንተም ባልንጀራህን ልትምረው አይገባህም ነበርን?’ በቍጣም ያለበትን ዕዳ ከፍሎ እስኪጨርስ ድረስ ለአሳሪዎች አሳልፎ ሰጠው።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች