ማቴዎስ 16:1-12

ማቴዎስ 16:1-12 NASV

ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ወደ ኢየሱስ ቀርበው ሊፈትኑት ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠየቁት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ምሽት ላይ፣ ‘ሰማዩ ስለ ቀላ ብራ ይሆናል’ ትላላችሁ፤ ንጋት ላይም፣ ‘ሰማዩ ቀልቷል፣ ከብዷልም፤ ስለዚህ ዝናብ ይዘንባል’ ትላላችሁ። የሰማዩን ገጽታ ትለያላችሁ፤ ነገር ግን የዘመኑን ምልክት መለየት አትችሉም። ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይፈልጋል፤ ነገር ግን ከዮናስ ምልክት በቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም።” ከዚያም ኢየሱስ ትቷቸው ሄደ። ባሕሩን እንደ ተሻገሩም፣ ደቀ መዛሙርቱ እንጀራ መያዝ ረስተው ነበር። ኢየሱስም፣ “ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠበቁ” አላቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው፣ “እንጀራ ስላልያዝን ነው” ተባባሉ። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ እምነት የጐደላችሁ፤ እርስ በርሳችሁ፣ እንጀራ ስለሌለን ነው በማለት የምትነጋገሩት ስለ ምንድን ነው? ዐምስቱ እንጀራ ለዐምስት ሺሕ ሰው በቅቶ ስንት መሶብ ተርፎ እንዳነሣችሁ አታስታውሱምን? እንዲሁም ሰባቱ እንጀራ ለአራት ሺሕ ሰው በቅቶ ስንት መሶብ ተርፎ እንዳነሣችሁ ልብ አላላችሁም ማለት ነውን? ታዲያ የነገርኋችሁ ስለ እንጀራ እንዳልሆነ እንዴት አታስተውሉም? አሁንም ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁ።” በዚህ ጊዜ ያስጠነቀቃቸው እንጀራ ውስጥ ስለሚጨመረው እርሾ ሳይሆን፣ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት መሆኑ ገባቸው።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች