ማቴዎስ 15:29-39

ማቴዎስ 15:29-39 NASV

ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ በገሊላ ባሕር አጠገብ ወዳለው ስፍራ በመሄድ ወደ ተራራ ወጥቶ ተቀመጠ። ቍጥሩ ብዙ የሆነ ሕዝብም ዐንካሶችን፣ ዐይነ ስውሮችን፣ ሽባዎችን፣ ዲዳዎችን እንዲሁም ሌሎች ብዙዎችን ሕመምተኞች ይዘው ወደ እርሱ በማምጣት በእግሮቹ ሥር አስቀመጧቸው፤ እርሱም ፈወሳቸው። ሕዝቡም ዲዳው ሲናገር፣ ሽባው ደኅና ሲሆን፣ ዐንካሳው ቀጥ ብሎ ሲሄድ፣ ዐይነ ስውሩም ሲያይ ተመልክተው ተደነቁ፤ የእስራኤልንም አምላክ አመሰገኑ። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሱ ጠርቶ፣ “ሕዝቡ ከእኔ ጋራ ሦስት ቀን ስለ ሆናቸውና የሚበሉት ስለሌላቸው ለእነዚህ ሰዎች ዐዝንላቸዋለሁ፤ በመንገድ ላይ በራብ ዝለው እንዳይወድቁ ጦማቸውን ልሰድዳቸው አልፈቅድም” አለ። ደቀ መዛሙርቱም፣ “በዚህ ምድረ በዳ ይህን ሁሉ ሕዝብ ለማብላት በቂ እንጀራ ከየት እናገኛለን?” አሉት። ኢየሱስም፣ “ለመሆኑ ስንት እንጀራ አላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “ሰባት እንጀራና ጥቂት ትንንሽ ዓሣ” አሉት። እርሱም ሕዝቡን መሬት ላይ እንዲቀመጡ አዘዛቸው፤ ሰባቱን እንጀራና ዓሣውን ይዞ ካመሰገነ በኋላ ቈርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ እነርሱም ለሕዝቡ አከፋፈሉ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ደቀ መዛሙርቱም የተረፈውን ቍርስራሽ ሰባት መሶብ ሙሉ አነሡ። የበሉትም ከሴቶችና ከሕፃናት ሌላ አራት ሺሕ ወንዶች ነበሩ። ኢየሱስ ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላ፣ ወደ ጀልባ ገብቶ ወደ መጌዶል ሄደ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች