ማቴዎስ 13:3-23

ማቴዎስ 13:3-23 NASV

ብዙ ነገሮችን በምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “አንድ ገበሬ ዘር ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም ሳለ፣ አንዳንዱ ዘር መንገድ ዳር ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው ለቅመው በሉት። አንዳንዱም ዘር በቂ ዐፈር በሌለበት በድንጋያማ መሬት ላይ ወደቀ፤ ዐፈሩ ጥልቀት ስላልነበረው ፈጥኖ በቀለ፤ ነገር ግን ፀሓይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ፤ ሥር ባለመስደዱም ደረቀ። ሌላው ዘር በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም አደገና ቡቃያውን ዐንቆ አስቀረው፤ ሌላውም ዘር ደግሞ በጥሩ መሬት ላይ ወደቀ፤ ፍሬም አፈራ፤ አንዱ መቶ፣ አንዱ ስድሳ፣ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!” ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “ለምን ለሕዝቡ በምሳሌ ትናገራለህ?” አሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማይን ምስጢር ማወቅ ተሰጥቷችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። ላለው ይጨመርለታል፤ ይትረፈረፍለታልም፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። ስለዚህ እንዲህ በማለት በምሳሌ የምነግራቸው ለዚህ ነው፤ “እያዩ፣ አያዩም፤ እየሰሙ፣ አይሰሙም ወይም አያስተውሉም፤ እንዲህ ተብሎ የተነገረው የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል፤ “ ‘መስማትንስ ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁ፤ ነገር ግን ልብ አትሉም። የሕዝቡ ልብ ደንድኗልና፤ ጆሯቸውም አይሰማም፤ እንዳያዩም ዐይናቸውን ጨፍነዋል፤ ይህ ባይሆን ኖሮ፣ በዐይናቸው አይተው፣ በጆሯቸው ሰምተው፣ በልባቸውም አስተውለው፣ ወደ እኔ በተመለሱና በፈወስኋቸው ነበር።’ የእናንተ ዐይኖች ስለሚያዩ፣ ጆሮዎቻችሁም ስለሚሰሙ ግን ብፁዓን ናቸው። እውነት እላችኋለሁ፤ ብዙ ነቢያትና ብዙ ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ለማየትና የምትሰሙትንም ለመስማት ተመኝተው ነበር፤ ግን አልሆነላቸውም። “እንግዲህ የዘሪውን ምሳሌ ስሙ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት ቃል ሰምቶ ከማያስተውል ከማንኛውም ሰው ልብ ውስጥ ክፉው መጥቶ የተዘራውን ዘር ይነጥቃል። ይህ እንግዲህ በመንገድ ዳር የተዘራው ዘር ነው። በጭንጫ መሬት ላይ የተዘራው፣ ቃሉን ሰምቶ ወዲያውኑ በደስታ የሚቀበለውን ሰው ይመስላል። ነገር ግን ሥር ባለመስደዱ ብዙ አይቈይም፤ በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት ሲመጣ ወዲያውኑ ይሰናከላል። በእሾኽ መካከል የተዘራው ዘር ቃሉን ሰምቶ ለዚህ ዓለም በመጨነቅና በብልጽግና ሐሳብ በመታለል ታንቆ ያላፈራን ሰው ይመስላል። በጥሩ መሬት ላይ የተዘራው ዘር ግን ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውለውን ሰው ይመስላል፤ በርግጥም ፍሬ ያፈራል፤ አንዱ መቶ፣ አንዱ ስድሳ፣ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች