ማቴዎስ 13:1-17

ማቴዎስ 13:1-17 NASV

በዚያ ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕሩ አጠገብ ተቀመጠ። ብዙ ሕዝብም ስለ ከበበው በባሕሩ ዳር ትቷቸው ጀልባ ላይ ወጥቶ ተቀመጠ። ብዙ ነገሮችን በምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “አንድ ገበሬ ዘር ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም ሳለ፣ አንዳንዱ ዘር መንገድ ዳር ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው ለቅመው በሉት። አንዳንዱም ዘር በቂ ዐፈር በሌለበት በድንጋያማ መሬት ላይ ወደቀ፤ ዐፈሩ ጥልቀት ስላልነበረው ፈጥኖ በቀለ፤ ነገር ግን ፀሓይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ፤ ሥር ባለመስደዱም ደረቀ። ሌላው ዘር በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም አደገና ቡቃያውን ዐንቆ አስቀረው፤ ሌላውም ዘር ደግሞ በጥሩ መሬት ላይ ወደቀ፤ ፍሬም አፈራ፤ አንዱ መቶ፣ አንዱ ስድሳ፣ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!” ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “ለምን ለሕዝቡ በምሳሌ ትናገራለህ?” አሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማይን ምስጢር ማወቅ ተሰጥቷችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። ላለው ይጨመርለታል፤ ይትረፈረፍለታልም፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። ስለዚህ እንዲህ በማለት በምሳሌ የምነግራቸው ለዚህ ነው፤ “እያዩ፣ አያዩም፤ እየሰሙ፣ አይሰሙም ወይም አያስተውሉም፤ እንዲህ ተብሎ የተነገረው የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል፤ “ ‘መስማትንስ ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁ፤ ነገር ግን ልብ አትሉም። የሕዝቡ ልብ ደንድኗልና፤ ጆሯቸውም አይሰማም፤ እንዳያዩም ዐይናቸውን ጨፍነዋል፤ ይህ ባይሆን ኖሮ፣ በዐይናቸው አይተው፣ በጆሯቸው ሰምተው፣ በልባቸውም አስተውለው፣ ወደ እኔ በተመለሱና በፈወስኋቸው ነበር።’ የእናንተ ዐይኖች ስለሚያዩ፣ ጆሮዎቻችሁም ስለሚሰሙ ግን ብፁዓን ናቸው። እውነት እላችኋለሁ፤ ብዙ ነቢያትና ብዙ ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ለማየትና የምትሰሙትንም ለመስማት ተመኝተው ነበር፤ ግን አልሆነላቸውም።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች