ከዚህ በኋላ በጋኔን የተያዘ ዕውርና ድዳ የሆነ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፤ ኢየሱስም ፈወሰው፤ ሰውየውም ማየትና መናገር ቻለ። ሕዝቡም ሁሉ ተደንቀው፣ “ይህ ሰው የዳዊት ልጅ ይሆንን?” አሉ። ነገር ግን ፈሪሳውያን ይህን በሰሙ ጊዜ፣ “ይህ ሰው አጋንንትን የሚያወጣው በአጋንንት አለቃ በብዔልዜቡል ብቻ መሆን አለበት” አሉ። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እርስ በርሱ የሚከፋፈል መንግሥት ሁሉ ይወድቃል፤ እርስ በርሱም የተከፋፈለ ከተማ ወይም ቤት አይጸናም። ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያስወጣ ከሆነ፣ እርስ በርሱ ተለያይቷል ማለት ነው፤ እንዲህ ከሆነ ደግሞ መንግሥቱ እንዴት ጸንቶ ሊቆም ይችላል? እኔ አጋንንትን የማስወጣው በብዔልዜቡል ከሆነ፣ ልጆቻችሁ በምን ሊያስወጧቸው ነው? ስለዚህ ልጆቻችሁ ይፈርዱባችኋል። እኔ ግን አጋንንትን የማስወጣው በእግዚአብሔር መንፈስ ከሆነ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ መጥታለች። “ወይስ አንድ ሰው ወደ ኀይለኛ ሰው ቤት ገብቶ ንብረቱን ለመዝረፍ ቢፈልግ፣ አስቀድሞ ያን ኀይለኛ ሰው ሳያስር እንዴት አድርጎ ይሳካለታል? ኋላም ቤቱን መበዝበዝ ይችላል። “ከእኔ ጋራ ያልሆነ ይቃወመኛል፤ ከእኔም ጋራ የማይሰበስብ ይበትናል። ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ኀጢአት መሥራትና የስድብ ቃል ሁሉ መናገር ለሰዎች ይቅር ይባልላቸዋል፤ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚነገር የስድብ ቃል ይቅር አይባልም። ማንም ሰው በሰው ልጅ ላይ የሚናገረው ክፉ ቃል ይቅር ይባላል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚናገረው ክፉ ቃል ግን በዚህም ሆነ በወዲያኛው ዓለም ይቅር አይባልም። “ዛፍ ሁሉ በፍሬው ስለሚታወቅ፣ መልካም ፍሬ እንድታገኙ መልካም ዛፍ ይኑራችሁ፤ መጥፎ ዛፍ ቢኖራችሁ ግን መጥፎ ፍሬ ታገኛላችሁ። እናንተ የእፉኝት ልጆች፤ እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳለ፣ መልካም ነገር መናገር እንዴት ትችላላችሁ? በልብ የሞላውን አንደበት ይናገረዋልና። መልካም ሰው በልቡ ካከማቸው መልካም ነገር መልካም ነገር ያወጣል፤ ክፉ ሰውም በልቡ ካከማቸው ክፉ ነገር መጥፎ ነገርን ያወጣል። ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰዎች ስለ ተናገሩት ከንቱ ቃል ሁሉ በፍርድ ቀን ይጠየቁበታል። ምክንያቱም ከቃልህ የተነሣ ትጸድቃለህ፤ ከቃልህም የተነሣ ይፈረድብሃልና።” ከዚያም አንዳንድ ፈሪሳውያንና የአይሁድ ሃይማኖት መምህራን፣ “መምህር ሆይ፤ ከአንተ ምልክት ማየት እንፈልጋለን” አሉት። እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይፈልጋል፤ ነገር ግን ከነቢዩ ዮናስ ምልክት በቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም። ዮናስ በትልቅ ዓሣ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ቈየ፣ እንዲሁ የሰው ልጅም ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በምድር ሆድ ውስጥ ይቈያል። የነነዌ ሰዎች በፍርድ ዕለት ከዚህ ትውልድ ጋራ ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ እነርሱ በዮናስ ስብከት ንስሓ ገብተዋልና። እነሆ፤ ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ። በፍርድ ዕለት የደቡብ ንግሥት ከዚህ ትውልድ ጋራ ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ መጥታለችና። እነሆ፤ ከሰሎሞን የሚበልጥ እዚህ አለ።
ማቴዎስ 12 ያንብቡ
ያዳምጡ ማቴዎስ 12
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማቴዎስ 12:22-42
12 ቀናት
ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ሰዎችን ሲፈውስ ኃይሉንና ርኅራኄውን ያሳየበትን መንገድ መርምር። አንድ አጭር ቪዲዮ ኢየሱስ በእያንዳንዱ ቀን የፈወሰውን ባለ 12 ክፍል እቅድ ጎላ አድርጎ ያሳያል።
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች