ሚልክያስ 4:1-6

ሚልክያስ 4:1-6 NASV

“እነሆ፤ እንደ ምድጃ እሳት የሚነድድ ቀን ይመጣል፤ ትዕቢተኞች ሁሉና ክፉ አድራጊዎች በሙሉ ገለባ ይሆናሉ፤ ያ የሚመጣው ቀንም ያቃጥላቸዋል” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። “ሥርም ሆነ ቅርንጫፍ አያስቀርላቸውም። ስሜን ለምትፈሩ ለእናንተ ግን የጽድቅ ፀሓይ በክንፎቿ ፈውስ ይዛ ትወጣለች፤ እናንተም እንደ ሠባ እንቦሳ እየቦረቃችሁ ትወጣላችሁ። እኔ በምሠራበት ቀን ክፉዎችን ትረግጣላችሁ፤ ከእግራችሁ ጫማ በታች ዐመድ ይሆናሉ” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። “ለእስራኤል ሁሉ ሕጎችና ሥርዐቶች ይሆኑ ዘንድ፣ ለአገልጋዬ ለሙሴ በኮሬብ የሰጠሁትን ሕግ አስቡ። “እነሆ፤ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ከመምጣቱ በፊት፣ ነቢዩ ኤልያስን እልክላችኋለሁ። መጥቼ ምድርን በርግማን እንዳላጠፋ፣ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፣ የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል።”