ሚልክያስ 3:1-10

ሚልክያስ 3:1-10 NASV

“እነሆ፤ በፊቴ መንገድ የሚያዘጋጅ መልእክተኛዬን እልካለሁ፤ የምትፈልጉት ጌታ በድንገት ወደ ቤተ መቅደሱ ይመጣል፤ ደስ የምትሰኙበትም የቃል ኪዳኑ መልእክተኛ ይመጣል” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። እርሱ የሚመጣበትን ቀን ማን ሊቋቋመው ይችላል? በሚገለጥበትስ ጊዜ በፊቱ መቆም የሚችል ማን ነው? እርሱ እንደ አንጥረኛ እሳት ወይም እንደ ልብስ ዐጣቢ ሳሙና ነውና። ብርን እንደሚያነጥርና እንደሚያነጻ ሰው ይቀመጣል፤ ሌዋውያንንም አንጽቶ እንደ ወርቅና እንደ ብር ያጠራቸዋል፤ ከዚያም እግዚአብሔር ቍርባንን በጽድቅ የሚያቀርቡ ሰዎች ይኖሩታል፤ በዚያ ጊዜ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ቍርባን እንዳለፉት ቀናትና እንደ ቀድሞው ዘመን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል። “ስለዚህ እኔ ለፍርድ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ በመተተኞች፣ በአመንዝራዎች፣ በሐሰት በሚምሉ፣ የሠራተኞችን ደመወዝ በሚከለክሉ፣ መበለቶችንና ድኻ አደጉን በሚጨቍኑ፣ መጻተኞችን ፍትሕ በሚነፍጉ፣ እኔንም በማይፈሩት ላይ እመሰክርባቸው ዘንድ እፈጥናለሁ” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። “እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፤ ስለዚህ እናንተ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፤ አልጠፋችሁም። ከአባቶቻችሁ ዘመን ጀምሮ ከትእዛዞቼ ፈቀቅ ብላችኋል፤ አልጠበቃችኋቸውምም፤ ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። “እናንተ ግን፣ ‘የምንመለሰው እንዴት ነው?’ ትላላችሁ። “ሰው እግዚአብሔርን ይሰርቃልን? እናንተ ግን ትሰርቁኛላችሁ። “እናንተ ግን፣ ‘እንዴት እንሰርቅሃለን?’ ትላላችሁ። “ዐሥራትና መባ ትሰርቁኛላችሁ፤ እናንተም፣ መላው ሕዝባችሁም ስለምትሰርቁኝ የተረገማችሁ ናችሁ። በቤቴ መብል እንዲኖር፣ እኔንም በዚህ እንድትፈትኑኝ ዐሥራቱን ሁሉ ወደ ጐተራ አስገቡ” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ “የሰማይን መስኮት የማልከፍትላችሁ፣ የተትረፈረፈ በረከትንም ማስቀመጫ እስክታጡ ድረስ የማላፈስስላችሁ ከሆነ ተመልከቱ።