በሚልክያስ በኩል ወደ እስራኤል የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ንግር ይህ ነው፤ “እኔ ወድጃችኋለሁ” ይላል እግዚአብሔር። “እናንተ ግን፣ ‘እንዴት ወደድኸን?’ ትላላችሁ።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ዔሳው የያዕቆብ ወንድም አልነበረምን? ያዕቆብን ወደድሁ፤ ዔሳውን ግን ጠላሁ፤ ተራሮቹን ባድማ አደረግሁ፤ ርስቱንም ለምድረ በዳ ቀበሮዎች ሰጠሁበት።” ኤዶምያስ፣ “ብንደመሰስም እንኳ የፈረሰውን መልሰን እንሠራዋለን” ይል ይሆናል። የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ግን እንዲህ ይላል፤ “እነርሱ ይሠሩ ይሆናል፤ እኔ ግን አፈርስባቸዋለሁ፤ ክፉ ምድር፣ እግዚአብሔርም ለዘላለም የተቈጣው ሕዝብ ተብለው ይጠራሉ። ይህንም በገዛ ዐይናችሁ ታያላችሁ፤ እናንተም፣ ‘ከእስራኤል ዳርቻ ወዲያ እንኳ እግዚአብሔር ታላቅ ነው!’ ትላላችሁ። “ልጅ አባቱን፣ ባሪያም ጌታውን ያከብራል፤ እኔ አባት ከሆንሁ፣ መከበሬ የት አለ? ጌታስ ከሆንሁ መፈራቴ የት አለ?” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። “ካህናት ሆይ፤ ስሜን የምታቃልሉት እናንተ ናችሁ። “እናንተ ግን፣ ‘ስምህን ያቃለልነው እንዴት ነው?’ ትላላችሁ። “በመሠዊያዬ ላይ የረከሰ ምግብ ታስቀምጣላችሁ። “እናንተ ግን፣ ‘ያረከስንህ እንዴት ነው?’ አላችሁ። “የእግዚአብሔር ገበታ የተናቀ ነው በማለታችሁ ነው። የታወረውን እንስሳ ለመሥዋዕት ስታቀርቡ፣ ያ በደል አይደለምን? ዐንካሳውን ወይም በሽተኛውን እንስሳ መሥዋዕት አድርጋችሁ ስታቀርቡ፣ ያስ በደል አይደለምን? ያንኑ ለገዣችሁ ብታቀርቡ፣ በእናንተ ደስ ይለዋልን? ወይስ ይቀበለዋልን?” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። “አሁን ግን እንዲራራልን እግዚአብሔርን ለምኑ፤ እንደዚህ ዐይነቱን መሥዋዕት ይዛችሁ ስትቀርቡ ይቀበላችኋልን?” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። “በመሠዊያዬ ላይ ከንቱ እሳት እንዳታነድዱ፣ ምነው ከእናንተ አንዱ የቤተ መቅደሱን ደጅ በዘጋ ኖሮ! እኔ በእናንተ ደስ አይለኝም፤ ከእጃችሁም ምንም ዐይነት ቍርባን አልቀበልም” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። “ከፀሓይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ፣ ስሜ በሕዝቦች መካከል የከበረ ይሆናል፤ በየስፍራውም ሁሉ ለስሜ ዕጣንና ንጹሕ ቍርባን ያቀርባሉ፤ ስሜ በሕዝቦች መካከል የከበረ ይሆናልና” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። “እናንተ ግን የእግዚአብሔር ገበታ፣ ‘ርኩስ ነው’ ምግቡም፣ ‘የተናቀ ነው’ በማለት ታቃልላላችሁ። ደግሞም፣ ‘ይህ ድካም ነው’ በማለት በንቀት ጢቅ አላችሁበት” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። “በቅሚያ የመጣውን፣ ዐንካሳውንና የታመመውን እንስሳ ቍርባን አድርጋችሁ ስታቀርቡ ከእጃችሁ መቀበል ይገባኛልን?” ይላል እግዚአብሔር፤ “በመንጋው ውስጥ ተቀባይነት ያለው ተባዕት በግ ኖሮት ይህንኑ ሊሰጥ ተስሎ ሳለ፣ በማታለል ነውር ያለበትን እንስሳ ለጌታ የሚሠዋ ርጉም ይሁን፤ እኔ ታላቅ ንጉሥ ነኝ፤ ስሜም በሕዝቦች ዘንድ ሊፈራ የሚገባ ነውና” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
ሚልክያስ 1 ያንብቡ
ያዳምጡ ሚልክያስ 1
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሚልክያስ 1:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች