ሉቃስ 9:37-42

ሉቃስ 9:37-42 NASV

በማግስቱም ከተራራው ከወረዱ በኋላ፣ ብዙ ሕዝብ መጥቶ ኢየሱስን አገኘው። በዚህ ጊዜ ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፤ “መምህር ሆይ፤ ያለኝ ልጅ እርሱ ብቻ ስለ ሆነ፣ ልጄን እንድታይልኝ እለምንሃለሁ። መንፈስ ሲይዘው በድንገት ይጮኻል፤ ዐረፋ እያስደፈቀው ያንፈራግጠዋል፤ ጕዳትም ካደረሰበት በኋላ በስንት መከራ ይተወዋል፤ ደቀ መዛሙርትህ እንዲያወጡለት ለመንኋቸው፤ ነገር ግን አልቻሉም።” ኢየሱስም “የማታምን ጠማማ ትውልድ ሆይ፤ እስከ መቼ ከእናንተ ጋራ እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ልጅህን ወደዚህ አምጣው!” አለ። ልጁ በመምጣት ላይ ሳለም ጋኔኑ መሬት ላይ ጥሎ አንፈራገጠው፤ ኢየሱስ ግን ርኩሱን መንፈስ ገሥጾ ልጁን ፈወሰው፤ ለአባቱም መልሶ ሰጠው።