ሉቃስ 9:1-17

ሉቃስ 9:1-17 NASV

ኢየሱስም ዐሥራ ሁለቱን ሐዋርያት ወደ ራሱ ጠርቶ አጋንንትን ሁሉ እንዲያወጡ፣ ደዌንም እንዲፈውሱ ኀይልና ሥልጣን ሰጣቸው፤ ደግሞም የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዲሰብኩና የታመሙትን እንዲፈውሱ ላካቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “ለመንገዳችሁ በትር፣ ከረጢት፣ እንጀራ፣ ገንዘብ፣ ወይም ትርፍ እጀ ጠባብ መያዝ አትያዙ። ከዚያ ከተማ እስከምትወጡ ድረስ መጀመሪያ በገባችሁበት በማንኛውም ቤት ቈዩ። የከተማው ሰዎች ሳይቀበሏችሁ ቀርተው ከተማቸውን ለቅቃችሁ ስትሄዱ፣ ምስክር እንዲሆንባቸው የእግራችሁን ትቢያ አራግፋችሁ ውጡ።” እነርሱም በዚሁ መሠረት ወጥተው ወንጌልን እየሰበኩ በየቦታው ሁሉ ሕመምተኞችን እየፈወሱ በየመንደሩ ያልፉ ነበር። የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስም፣ በዚህ ጊዜ የሆነውን ነገር ሁሉ ሰምቶ በሁኔታው ተደናገረ፤ ምክንያቱም አንዳንድ ሰዎች ዮሐንስ ከሙታን እንደ ተነሣ ያወሩ ነበር፤ ሌሎች ኤልያስ እንደ ተገለጠ፣ ሌሎች ደግሞ ከቀድሞዎቹ ነቢያት አንዱ ከሙታን እንደ ተነሣ ይናገሩ ነበር። ሄሮድስም፣ “መጥምቁ ዮሐንስን እኔው ራሴ ዐንገቱን አስቈርጬው ሞቷል፤ ታዲያ፣ ስለ እርሱ እንዲህ ሲወራ የምሰማው ይህ ሰው ማነው?” አለ፤ በዐይኑም ሊያየው ይሻ ነበር። ሐዋርያትም ተመልሰው በመጡ ጊዜ ያደረጉትን ሁሉ ነገሩት፤ እርሱም ይዟቸው ቤተ ሳይዳ ወደምትባል ከተማ በመሄድ ለብቻው ገለል አለ። ሕዝቡም ይህንኑ ዐውቀው ተከተሉት፤ እርሱም ተቀብሏቸው ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ይነግራቸው ነበር፤ ፈውስ የሚያስፈልጋቸውንም ፈወሳቸው። ቀኑም ሊመሽ ሲል፣ ዐሥራ ሁለቱ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “ያለነው በምድረ በዳ ስለ ሆነ፣ ሕዝቡ ወደ አካባቢው መንደርና ገጠር ሄደው ማደሪያና ምግብ እንዲፈልጉ አሰናብታቸው” አሉት። እርሱ ግን፣ “የሚበሉትን እናንተው ስጧቸው” አላቸው። እነርሱም፣ “ለዚህ ሁሉ ሕዝብ የሚበቃ ምግብ ሄደን ካልገዛን በቀር፣ እኛ ያለን ከዐምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ አይበልጥም” አሉት፤ ዐምስት ሺሕ ያህል ወንዶች በዚያ ነበሩና። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን፣ “ሕዝቡን በዐምሳ፣ በዐምሳ ሰው መድባችሁ አስቀምጧቸው” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም በታዘዙት መሠረት ሰዎቹ እንዲቀመጡ አደረጉ። እርሱም ዐምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ እያየ ባረካቸው፤ ቈርሶም ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ከእነርሱ የተረፈውን ቍርስራሽ እንጀራ ዐሥራ ሁለት መሶብ አነሡ።