ከዚህ በኋላ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ቃል እየሰበከ በየከተማውና በየመንደሩ ዐለፈ። ዐሥራ ሁለቱም ከርሱ ጋራ ነበሩ፤ እንዲሁም ከርኩሳን መናፍስትና ከደዌ የተፈወሱ አንዳንድ ሴቶች ዐብረውት ነበሩ፤ እነርሱም ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት የተባለችው ማርያም፣ የሄሮድስ ቤት ኀላፊ የነበረው የኩዛ ሚስት ዮሐና፣ ሶስና፣ ደግሞም ሌሎች ብዙዎች ነበሩ፤ እነዚህም በግል ንብረታቸው የሚያገለግሉት ነበሩ። ብዙ ሕዝብ በአንድነት ተሰብስቦ ሳለ፣ ደግሞም ሰዎች ከተለያዩ ከተሞች ወደ እርሱ በሚጐርፉበት ጊዜ፣ ይህን ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “አንድ ዐራሽ ዘሩን ሊዘራ ወጣ፤ ሲዘራም፣ አንዳንዱ ዘር መንገድ ዳር ወደቀ፣ በእግርም ተረጋገጠ፤ የሰማይ ወፎችም በሉት። አንዳንዱም ዘር በድንጋያማ ቦታ ላይ ወደቀ፤ እንደ በቀለም ርጥበት አልነበረውምና ደረቀ። ሌላው ዘር ደግሞ በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም ዐብሮት አደገና ዐንቆ አስቀረው። ሌላውም ዘር በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ መቶ ዕጥፍ አፈራ።” ይህን ብሎ ሲያበቃም ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ” አለ። ደቀ መዛሙርቱም የዚህን ምሳሌ ትርጕም ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ምስጢር ማወቅ ለእናንተ ተሰጥቷል፤ ለሌሎች ግን በምሳሌ እናገራለሁ፤ ይኸውም፣ “ ‘እያዩ ልብ እንዳይሉ፣ እየሰሙም እንዳያስተውሉ ነው።’ “እንግዲህ የምሳሌው ትርጕም ይህ ነው፤ ዘር የተባለው የእግዚአብሔር ቃል ነው። በመንገድ ዳር የወደቀው ቃሉን የሚሰሙ፣ ነገር ግን አምነው እንዳይድኑ ዲያብሎስ መጥቶ ቃሉን ከልባቸው የሚወስድባቸው ናቸው። በድንጋያማ ቦታ ላይ የወደቀውም ቃሉን ሲሰሙ በደስታ የሚቀበሉ ናቸው፤ እነዚህ ለጊዜው ያምናሉ እንጂ ሥር ስለሌላቸው በፈተና ጊዜ ፈጥነው የሚክዱ ናቸው። በእሾኽ መካከል የወደቀውም ቃሉን የሚሰሙት ናቸው፤ እነዚህም ውለው ዐድረው በምድራዊ ሕይወት ጭንቀት፣ በባለጠግነትና ተድላ ደስታ ታንቀው በሚገባ አያፈሩም። በመልካም መሬት ላይ የወደቀውም ቃሉን ቅንና በጎ በሆነ ልብ ሰምተው የሚጠብቁ፣ ታግሠውም በመጽናት ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው። “መብራትን አብርቶ በጋን ውስጥ ወይም ከዐልጋ ሥር የሚያስቀምጥ ማንም የለም፤ ይልቁንም ወደ ቤት የሚገቡ ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጠዋል። የማይገለጥ የተሰወረ፣ የማይታወቅ ወደ ብርሃን የማይወጣ፣ የተደበቀ ነገር የለምና። እንግዲህ እንዴት እንደምትሰሙ ተጠንቀቁ፤ ላለው ሁሉ ይጨመርለታልና፤ ከሌለው ሁሉ ግን ያው ያለው የሚመስለው እንኳ ይወሰድበታል።” ከዚህ በኋላ የኢየሱስ እናትና ወንድሞቹ እርሱ ወዳለበት መጡ፤ እነርሱም ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ወደ እርሱ ሊቀርቡ አልቻሉም። በዚህ ጊዜ፣ “እናትህና ወንድሞችህ ሊያዩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል” የሚል ወሬ ደረሰው። እርሱም መልሶ፣ “እናቴና ወንድሞቼስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚያደርጉት ናቸው” አላቸው። ከዕለታቱ በአንድ ቀን፣ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ጀልባ ላይ ወጣ፤ ኢየሱስም፤ “ወደ ባሕሩ ማዶ እንሻገር” አላቸው፤ ከዚያም ጕዞ ቀጠሉ። እየተጓዙ ሳሉም ኢየሱስ እንቅልፍ ወስዶት ተኛ፤ በዚህ ጊዜ በባሕሩ ላይ ማዕበል ተነሣ፤ ውሃውም ጀልባዋን ዘልቆ ስለ ገባ፣ አደጋ አፋፍ ላይ ደረሱ። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው፣ “ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ መጥፋታችን እኮ ነው!” እያሉ ቀሰቀሱት። እርሱም ነቅቶ ነፋሱንና የውሃውን መናወጥ ገሠጸ፤ በዚህ ጊዜ ነፋሱም ነውጡም ተወ፤ ጸጥታም ሆነ። እርሱም ደቀ መዛሙርቱን፣ “እምነታችሁ የት አለ?” አላቸው። እነርሱም በፍርሀትና በመደነቅ፣ “ይህ ነፋስንና ውሃን የሚያዝዝ፣ እነርሱም የሚታዘዙለት እርሱ ማን ነው?” ተባባሉ።
ሉቃስ 8 ያንብቡ
ያዳምጡ ሉቃስ 8
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሉቃስ 8:1-25
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች