የዮሐንስ መልእክተኞች ከሄዱ በኋላ፣ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ይናገር ጀመር፤ እንዲህም አለ፤ “ወደ በረሓ የወጣችሁት ምን ልታዩ ነው? ነፋስ የሚያወዛውዘውን ሸንበቆ? እኮ! ምን ልታዩ ወጣችሁ? ያማረ ልብስ የለበሰውን ሰው ነውን? ባማረ ልብስ የሚሽሞነሞኑና በድሎት የሚኖሩ በቤተ መንግሥት አሉላችሁ። ታዲያ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን ልታዩ? አዎን፣ እላችኋለሁ፤ ከነቢይም የሚበልጠውን ነው። እንዲህ ተብሎ የተጻፈለት እርሱ ነው፤ “ ‘መንገድህን በፊትህ የሚያዘጋጅ መልእክተኛዬን ከአንተ አስቀድሜ እልካለሁ።’ እላችኋለሁ፤ ከሴት ከተወለዱት መካከል ከዮሐንስ የሚበልጥ የለም፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል።” ቀረጥ ሰብሳቢዎች እንኳ ሳይቀሩ፣ ይህን የሰሙ ሁሉ፣ የዮሐንስን ጥምቀት በመጠመቅ ለእግዚአብሔር ተገቢውን ክብር ሰጡ፤ ፈሪሳውያንና ሕግ ዐዋቂዎች ግን በዮሐንስ እጅ ባለመጠመቃቸው፣ እግዚአብሔር ለእነርሱ ያለውን ዐላማ አቃለሉ። ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ የዚህን ትውልድ ሰዎች በምን ልመስላቸው? ምንስ ይመስላሉ? በገበያ ቦታ ተቀምጠው እርስ በርሳቸው እየተጠራሩ እንዲህ የሚባባሉ ልጆችን ይመስላሉ፤ “ ‘ዋሽንት ነፋንላችሁ፤ አልጨፈራችሁም፤ ሙሾ አወረድንላችሁ፤ አላለቀሳችሁም።’ ምክንያቱም መጥምቁ ዮሐንስ እህል ሳይበላና የወይን ጠጅ ሳይጠጣ ቢመጣ፣ ጋኔን አለበት አላችሁት፤ የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፣ ‘በልቶ የማይጠገብና ጠጪ፣ የቀረጥ ሰብሳቢዎችና የኀጢአተኞች ወዳጅ’ አላችሁት። ጥበብ ግን ትክክለኛ መሆኗ በልጆቿ ሁሉ ዘንድ ተረጋገጠ።” ከዚህ በኋላ ከፈሪሳውያን አንዱ ምግብ ዐብሮት እንዲበላ ኢየሱስን ጋበዘው፤ እርሱም ወደ ፈሪሳዊው ቤት ሄዶ በማእድ ተቀመጠ። በዚያ ከተማ የምትኖር አንዲት ኀጢአተኛ ሴት፣ ኢየሱስ በፈሪሳዊው ቤት በማእድ መቀመጡን በሰማች ጊዜ፣ አንድ የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ሽቱ ይዛ መጣች። ከበስተኋላው እግሮቹጋ ሆና እያለቀሰች እግሮቹን በእንባዋ ታርስ፣ በራሷም ጠጕር ታብሰው ጀመር፤ እግሮቹንም እየሳመች ሽቱውን ቀባችው። የጋበዘውም ፈሪሳዊ ይህን ባየ ጊዜ፣ “ይህ ሰው ነቢይ ቢሆን ኖሮ፣ የነካችው ሴት ማን እንደ ሆነች፣ ደግሞም ምን ዐይነት ሰው እንደ ሆነች ባወቀ ነበር፤ ኀጢአተኛ ናትና” ብሎ በልቡ ዐሰበ። ኢየሱስም፣ “ስምዖን ሆይ፤ የምነግርህ ነገር አለኝ” አለው። እርሱም፣ “መምህር ሆይ፤ ንገረኝ” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “ከአንድ አበዳሪ ገንዘብ የተበደሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ አንደኛው ዐምስት መቶ ዲናር፣ ሁለተኛው ደግሞ ዐምሳ ዲናር ነበረበት። የሚከፍሉትም ቢያጡ ዕዳቸውን ለሁለቱም ተወላቸው። እንግዲህ ከሁለቱ አበዳሪውን አብልጦ የሚወድደው የትኛው ነው?” ስምዖንም፣ “ብዙው ዕዳ የተተወለት ይመስለኛል” ሲል መለሰ። ኢየሱስም፣ “ትክክል ፈርደሃል” አለው። ወደ ሴቲቱም ዘወር ብሎ ስምዖንን እንዲህ አለው፤ “ይህችን ሴት ታያታለህን? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ፤ አንተ ለእግሮቼ ውሃ እንኳ አላቀረብህልኝም፤ እርሷ ግን እግሮቼን በእንባዋ እያራሰች በጠጕሯ አበሰች። አንተ ከቶ አልሳምኸኝም፤ እርሷ ግን ከገባሁ ጀምራ እግሮቼን ከመሳም አላቋረጠችም። አንተ ራሴን ዘይት አልቀባህም፤ እርሷ ግን እግሮቼን ሽቱ ቀባች። ስለዚህ እልሃለሁ፤ በብዙ ወድዳለችና ብዙው ኀጢአቷ ተሰርዮላታል፤ በትንሹ የተሰረየለት ግን የሚወድደው በትንሹ ነው።” ኢየሱስም ሴቲቱን፣ “ኀጢአትሽ ተሰርዮልሻል” አላት። ዐብረውት በማእድ ተቀምጠው የነበሩ እንግዶችም፣ “ይህ ኀጢአትን እንኳ የሚያስተሰርይ እርሱ ማን ነው?” ብለው በልባቸው አሰቡ። ኢየሱስም ሴቲቱን፣ “እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ” አላት።
ሉቃስ 7 ያንብቡ
ያዳምጡ ሉቃስ 7
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሉቃስ 7:24-50
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች