ሉቃስ 7:1-23

ሉቃስ 7:1-23 NASV

ኢየሱስ ይህን ሁሉ በሕዝቡ ፊት ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ገባ። በዚያም አንድ የመቶ አለቃ ነበረ፤ እጅግ የሚወድደው ባሪያውም ታምሞበት ለሞት ተቃርቦ ነበር። እርሱም ስለ ኢየሱስ በሰማ ጊዜ፣ ባሪያውን መጥቶ እንዲፈውስለት ይለምኑት ዘንድ አንዳንድ የአይሁድ ሽማግሌዎችን ላከበት። መልእክተኞቹም ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ እንዲህ ብለው አጥብቀው ለመኑት፤ “ይህን ልታደርግለት ይገባዋል፤ ምክንያቱም ይህ ሰው ሕዝባችንን ይወድዳል፤ ምኵራባችንንም ያሠራልን እርሱ ነው።” ኢየሱስም ከእነርሱ ጋራ ሄደ። እርሱም ወደ ቤቱ በተቃረበ ጊዜ፣ የመቶ አለቃው ወዳጆቹን ልኮ እንዲህ አለው፤ “ጌታ ሆይ፤ ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ የሚገባኝ ሰው አይደለሁምና አትድከም፤ ከዚህም የተነሣ በአንተ ፊት ለመቅረብ እንኳ እንደሚገባኝ ራሴን አልቈጠርሁም፤ ብቻ አንድ ቃል ተናገር፤ ብላቴናዬም ይፈወሳል። እኔ ራሴ የበላይ አለቃ አለኝ፤ ከበታቼም የማዝዛቸው ወታደሮች አሉኝ፤ አንዱን፣ ‘ሂድ’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውን፣ ‘ና’ ስለው ይመጣል፤ ባሪያዬንም፣ ‘ይህን አድርግ’ ስለው ያደርጋል።” ኢየሱስም ይህን ሲሰማ በርሱ ተደነቀ፤ ዘወር ብሎም ይከተለው ለነበረው ሕዝብ፣ “እላችኋለሁ፤ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት በእስራኤል እንኳ አላገኘሁም” አላቸው። የተላኩት ሰዎችም ወደ ቤት በተመለሱ ጊዜ፣ ባሪያውን ድኖ አገኙት። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ብዙ ሳይቈይ፣ ናይን ወደምትባል ከተማ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱና ብዙ ሕዝብም ዐብረውት ሄዱ። ወደ ከተማዋ መግቢያ በር ሲደርስም፣ እነሆ፤ ሰዎች የአንድ ሰው አስከሬን ተሸክመው ከከተማዋ ወጡ፤ ሟቹም ለእናቱ አንድ ልጅ ብቻ ነበር፤ እናቱም መበለት ነበረች፤ ብዙ የከተማውም ሕዝብ ከርሷ ጋራ ነበረ። ጌታም ባያት ጊዜ ራራላትና፣ “አይዞሽ፤ አታልቅሺ” አላት። ቀረብ ብሎም ቃሬዛውን ነካ፤ የተሸከሙትም ሰዎች ቀጥ ብለው ቆሙ፤ ኢየሱስም፣ “አንተ ጐበዝ፤ ተነሥ እልሃለሁ!” አለው። የሞተውም ሰው ቀና ብሎ ተቀመጠ፤ መናገርም ጀመረ። ኢየሱስም ወስዶ ለእናቱ ሰጣት። ሁሉም በፍርሀት ተውጠው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ፣ “ታላቅ ነቢይ በመካከላችን ተነሥቷል፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን ጐብኝቷል” አሉ። ይህም የኢየሱስ ዝና በመላው ይሁዳና በአካባቢው ባለው አገር ሁሉ ወጣ። የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም ይህን ሁሉ ለዮሐንስ ነገሩት። እርሱም ከመካከላቸው ሁለቱን ወደ ራሱ ጠርቶ፣ “ይመጣል የተባለልህ አንተ ነህ ወይስ ሌላ እንጠብቅ? በሉት” ብሎ ወደ ጌታ ላካቸው። ሰዎቹም ወደ ኢየሱስ መጥተው፣ “መጥምቁ ዮሐንስ፣ ‘ይመጣል የተባለልህ አንተ ነህ? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?’ ብሎ ወደ አንተ ልኮናል” አሉት። በዚያ ጊዜ ኢየሱስ ብዙ ሰዎችን ከበሽታ፣ ከደዌና ከርኩሳን መናፍስት ፈወሳቸው፤ የብዙ ዐይነ ስውራንንም ዐይን አበራ። ከዮሐንስ ተልከው የመጡትንም እንዲህ አላቸው፤ “ሄዳችሁ ያያችሁትንና የሰማችሁትን ለዮሐንስ ንገሩት፤ ዐይነ ስውራን ያያሉ፤ ዐንካሶች ይራመዳሉ፤ ለምጻሞች ይነጻሉ፤ ደንቈሮዎች ይሰማሉ፤ ሙታን ይነሣሉ፤ ለድኾችም ወንጌል ይሰበካል፤ በእኔ የማይሰናከል ሁሉ ብፁዕ ነው።”