ሉቃስ 5:3-11

ሉቃስ 5:3-11 NASV

ከጀልባዎቹም መካከል የስምዖን ወደ ነበረችው ገብቶ፣ ከምድር ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጋት ለመነው፤ ከዚያም ጀልባዋ ላይ ተቀምጦ ሕዝቡን ያስተምር ጀመር። ንግግሩን በጨረሰ ጊዜ ስምዖንን፣ “ወደ ጥልቁ ውሃ ፈቀቅ በልና ዓሣ ለመያዝ መረባችሁን ጣሉ” አለው። ስምዖንም መልሶ፣ “መምህር ሆይ፤ ሌሊቱን ሙሉ ስንደክም ዐድረን ምንም አልያዝንም፤ አንተ ካልህ ግን መረቦቹን እጥላለሁ” አለው። እንደዚያም ባደረጉ ጊዜ እጅግ ብዙ ዓሣ ያዙ፤ መረባቸውም ይበጣጠስ ጀመር። በሌላ ጀልባ የነበሩት ባልንጀሮቻቸው መጥተው እንዲያግዟቸውም በምልክት ጠሯቸው፤ እነርሱም መጥተው ሁለቱን ጀልባዎች በዓሣ ሞሏቸው፣ ጀልባዎቹም መስመጥ ጀመሩ። ስምዖን ጴጥሮስም ይህን ባየ ጊዜ በኢየሱስ ጕልበት ላይ ወድቆ፣ “ጌታ ሆይ፤ እኔ ኀጢአተኛ ሰው ነኝና ከእኔ ተለይ” አለው። ይህን ያለው እርሱና ከርሱ ጋራ የነበሩት በያዙት ዓሣ ብዛት ስለ ተደነቁ ነው፤ ደግሞም የስምዖን ባልንጀሮች የነበሩት የዘብዴዎስ ልጆች፣ ያዕቆብና ዮሐንስም ተደነቁ። ኢየሱስም ስምዖንን፣ “አትፍራ፤ ከእንግዲህ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ” አለው። እነርሱም ጀልባዎቹን ወደ ምድር ካስጠጉ በኋላ፣ ሁሉን ትተው ተከተሉት።