በምኵራብም የርኩስ ጋኔን መንፈስ ያደረበት ሰው ነበረ፤ እርሱም ከፍ ባለ ድምፅ ጮኾ፣ “ወዮ! የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፤ ምን የሚያገናኘን ጕዳይ አለ? የመጣኸው ልታጠፋን ነውን? አንተ ማን እንደ ሆንህ ዐውቃለሁ፤ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ!” አለው። ኢየሱስም፣ “ጸጥ በል፤ ከርሱም ውጣ!” ብሎ ገሠጸው። ጋኔኑም ሰውየውን በሕዝቡ ሁሉ ፊት ጣለውና ምንም ጕዳት ሳያደርስበት ለቅቆት ከርሱ ወጣ። ሁሉም ተገረሙ፤ እርስ በርሳቸውም፣ “ለመሆኑ ይህ ትምህርት ምንድን ነው? በሥልጣንና በኀይል ርኩሳን መናፍስትን ያዝዛል፤ እነርሱም እኮ ይወጣሉ” ተባባሉ። የእርሱም ዝና በአካባቢው ወዳለው ስፍራ ሁሉ ወጣ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከምኵራብ ወጥቶ ወደ ስምዖን ቤት ገባ። የስምዖንም ዐማት ኀይለኛ ትኵሳት ይዟት ታምማ ነበር፤ እንዲፈውሳትም ስለ እርሷ ለመኑት። እርሱም ወደ ተኛችበት ጠጋ ብሎ በማጐንበስ ትኵሳቱን ገሠጸው፤ ትኵሳቱም ለቀቃትና ወዲያው ተነሥታ አስተናገደቻቸው። ፀሓይ መጥለቂያ ላይም፣ የተለያየ ሕመም ያደረባቸውን ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤ እርሱም በእያንዳንዳቸው ላይ እጁን ጭኖ ፈወሳቸው። አጋንንትም ደግሞ፣ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ!” እያሉና እየጮኹ ከብዙ ሰዎች ወጡ። እርሱ ግን ገሠጻቸው፤ ክርስቶስ መሆኑንም ያውቁ ስለ ነበር፣ አንዳች እንዲናገሩ አልፈቀደላቸውም። ሲነጋም ኢየሱስ ወደ ምድረ በዳም ሄደ፤ ሕዝቡም ይፈልጉት ነበር፤ እርሱ ወዳለበትም ቦታ መጡ፤ ከእነርሱ ተለይቶ እንዳይሄድ ሊከለክሉት ሞከሩ። እርሱ ግን፣ “ወደ ሌሎቹም ከተሞች ሄጄ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል መስበክ ይገባኛል፤ የተላክሁት ለዚሁ ዐላማ ነውና” አላቸው። በይሁዳም በምኵራቦች መስበኩን ቀጠለ።
ሉቃስ 4 ያንብቡ
ያዳምጡ ሉቃስ 4
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሉቃስ 4:33-44
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች