ሉቃስ 23:1-56

ሉቃስ 23:1-56 NASV

በዚያ የተሰበሰቡት በሙሉ ተነሥተው ኢየሱስን ወደ ጲላጦስ ወሰዱት፤ እንዲህም እያሉ ይከስሱት ጀመር፤ “ይህ ሰው ሕዝባችንን ሲያስት፣ ለቄሳር ግብር እንዳይከፈል ሲከለክል፣ ደግሞም፣ ‘እኔ ክርስቶስ ንጉሥ ነኝ’ ሲል አገኘነው።” ጲላጦስም፣ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “አንተው አልህ” አለው። ጲላጦስም ለካህናት አለቆችና ለሕዝቡ፣ “እኔ በዚህ ሰው ላይ ምንም ወንጀል አላገኘሁበትም” አለ። እነርሱ ግን፣ “ይህ ሰው ከገሊላ ጀምሮ እዚህ ድረስ መላውን ይሁዳ ሳይቀር እያወከ ነው” እያሉ አጽንተው ተናገሩ። ጲላጦስም ይህን ሲሰማ፣ ሰውየው የገሊላ ሰው መሆኑን ለማረጋገጥ ጠየቀ፤ ኢየሱስ ከሄድሮስ ግዛት የመጣ መሆኑን ጲላጦስ ባወቀ ጊዜ፣ ሄሮድስ በዚያ ወቅት በኢየሩሳሌም ስለ ነበረ ወደ እርሱ ላከው። ሄሮድስም ኢየሱስን ብዙ ጊዜ ሊያየው ይፈልግ ስለ ነበር፣ ባየው ጊዜ እጅግ ደስ አለው፤ ስለ እርሱ ሰምቶ ስለ ነበር፣ ታምራት ሲሠራ ለማየት ተስፋ ያደርግ ነበር። ብዙ ጥያቄዎችንም አቀረበለት፤ እርሱ ግን ምንም አልመለሰለትም። የካህናት አለቆችና ጸሐፍትም እዚያው ቆመው በብርቱ ይወነጅሉት ነበር። ሄሮድስም ከወታደሮቹ ጋራ ናቀው፤ አፌዙበትም፤ የክብር ልብስ አልብሶም ወደ ጲላጦስ መልሶ ሰደደው። ሄሮድስና ጲላጦስም በዚሁ ዕለት ተወዳጁ፤ ቀደም ሲል ግን በመካከላቸው ጥል ነበረ። ጲላጦስም የካህናት አለቆችን፣ ገዦችንና ሕዝቡን በአንድነት ሰብስቦ፣ እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ሰው ሕዝቡን ለዐመፅ ያነሣሣል ብላችሁ ወደ እኔ አምጥታችሁት ነበር፤ እኔም በእናንተው ፊት መርምሬው፣ ባቀረባችሁበት ክስ አንዳች ወንጀል አላገኘሁበትም። ደግሞም ሄሮድስ እንዲሁ ምንም ስላላገኘበት ወደ እኛ መልሶታል፤ እንደምታዩት ይህ ሰው ለሞት የሚያበቃ ምንም ነገር አልፈጸመም፤ ስለዚህ ቀጥቼ እፈታዋለሁ።” [ይህን ያለው በበዓሉ አንድ እስረኛ እንዲፈታላቸው የግድ ያስፈልግ ስለ ነበረ ነው።] ሕዝቡም ሁሉ በአንድ ላይ፣ “ይህን ሰው ወዲያ አስወግደው! በርባንን ፍታልን!” እያሉ ጮኹ፤ በርባንም በከተማ ውስጥ የሕዝብ ዐመፅ በማነሣሣትና በነፍስ ግድያ የታሰረ ሰው ነበር። ጲላጦስም ኢየሱስን ሊፈታው ስለ ፈለገ፣ እንደ ገና ተናገራቸው፤ እነርሱ ግን፣ “ስቀለው! ስቀለው!” እያሉ ይጮኹ ነበር። ጲላጦስም ሦስተኛ ጊዜ፣ “ለምን? ይህ ሰው ምን የፈጸመው ወንጀል አለ? እኔ ለሞት የሚያበቃ ምንም በደል አላገኘሁበትም፤ ስለዚህ ቀጥቼ እፈታዋለሁ” አላቸው። እነርሱ ግን ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ እንዲሰቀል አጥብቀው ለመኑት፤ ጩኸታቸውም በረታ። ስለዚህ ጲላጦስ የጠየቁት እንዲፈጸም ውሳኔ አስተላለፈ። የሕዝብ ዐመፅ በማነሣሣትና በነፍስ ግድያ ታስሮ የነበረውን፣ እንዲፈታላቸውም የለመኑትን ያን ሰው ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን እንዳሻቸው እንዲያደርጉት አሳልፎ ሰጣቸው። ኢየሱስንም ይዘው ሲወስዱት፣ ስምዖን የተባለውን የቀሬና ሰው ከገጠር ሲመጣ አግኝተው መስቀሉን አሸክመው ኢየሱስን ተከትሎ እንዲሄድ አስገደዱት። ብዙ ሕዝብና ደረታቸውን እየደቁ የሚያለቅሱለት ሴቶችም ከኋላው ይከተሉት ነበር። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የኢየሩሳሌም ሴቶች፤ ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ እንጂ ለእኔ አታልቅሱ፤ እነሆ፤ ‘መካኖችና ያልወለዱ ማሕፀኖች፣ ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዓን ናቸው’ የምትሉበት ጊዜ ይመጣልና። በዚያ ጊዜ፣ “ ‘ተራሮችን፣ “ውደቁብን!” ኰረብቶችንም፣ “ሸፍኑን!” ’ ይላሉ። እንግዲህ በርጥብ ዕንጨት እንዲህ ካደረጉ፣ በደረቁ ምን ያደርጉ ይሆን?” ከርሱ ጋራ እንዲገደሉ ሌሎች ሁለት ወንጀለኞችን ወሰዷቸው። ቀራንዮ የተባለ ቦታ በደረሱ ጊዜ ሰቀሉት፤ ወንጀለኞቹንም አንዱን በቀኙ፣ ሌላውን በግራው ሰቀሏቸው። ኢየሱስም፣ “አባት ሆይ፤ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” አለ። እነርሱም ልብሱን በዕጣ ተከፋፈሉት። ሕዝቡም ቆመው ይመለከቱ ነበር። ገዦችም፣ “ሌሎችን አዳነ፤ በእግዚአብሔር የተመረጠው ክርስቶስ እርሱ ከሆነ፣ እስኪ ራሱን ያድን” እያሉ አፌዙበት። ወታደሮችም ቀርበው ያፌዙበት ነበር፤ የኮመጠጠ የወይን ጠጅ እየሰጡትም፣ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ከሆንህ፣ ራስህን አድን” ይሉት ነበር። ከራሱም በላይ፣ “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ነው” የሚል ጽሑፍ ነበር። ከተሰቀሉት ወንጀለኞችም አንዱ እየተሳደበ፣ “አንተ ክርስቶስ አይደለህምን? እስኪ፣ ራስህንም እኛንም አድን” ይለው ነበር። ሌላው ወንጀለኛ ግን እንዲህ ሲል ገሠጸው፤ “ተመሳሳይ ፍርድ እየተቀበልህ ሳለህ፣ ከቶ እግዚአብሔርን አትፈራምን? እኛ ላደረግነው ነገር ቅጣት እየተቀበልን ስለ ሆነ፣ ተገቢ ፍርድ ላይ ነን፤ ይህ ሰው ግን አንዳች ክፉ ነገር አላደረገም።” ደግሞም፣ “ኢየሱስ ሆይ፤ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ” አለው። ኢየሱስም፣ “እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋራ በገነት ትሆናለህ” አለው። ጊዜው ስድስት ሰዓት ያህል ነበር፤ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስም በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ፤ የፀሓይ ብርሃን ተከልክሏልና። የቤተ መቅደሱም መጋረጃ ተቀድዶ ለሁለት ተከፈለ። ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኸ፣ “አባት ሆይ፤ መንፈሴን በእጅህ እሰጣለሁ” አለ፤ ይህንም ብሎ ሞተ። የመቶ አለቃውም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ፣ “ይህ ሰው በርግጥ ጻድቅ ነበር” ብሎ እግዚአብሔርን አመሰገነ። ይህንኑ ለማየት በስፍራው ተሰብስበው የነበሩ ሰዎችም ሁሉ የሆነውን ነገር በተመለከቱ ጊዜ ደረታቸውን እየደቁ ተመለሱ። ነገር ግን ኢየሱስን በቅርብ የሚያውቁት ሁሉ እንዲሁም ከገሊላ ጀምሮ የተከተሉት ሴቶች ይህን እየተመለከቱ ከሩቅ ቆመው ነበር። የአይሁድ ሸንጎ አባል የሆነ፣ አንድ ዮሴፍ የሚባል በጎና ጻድቅ ሰው ነበር። ይህ ሰው በሸንጎው ምክርና ድርጊት አልተባበረም ነበር፤ እርሱም አርማትያስ የምትባል የአይሁድ ከተማ ሰው ሲሆን፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት መምጣት ይጠባበቅ ነበር። ይህም ሰው ወደ ጲላጦስ ሄዶ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው፤ በተፈቀደለትም ጊዜ፣ ሥጋውን አውርዶ በበፍታ ከፈነው፤ ከድንጋይ ተፈልፍሎ በተሠራና ገና ማንም ባልተቀበረበት መቃብር ውስጥ አስቀመጠው። ዕለቱ ሰንበት ሊገባ ስለ ነበር፣ የመዘጋጃ ቀን ነበረ። ከገሊላ ጀምሮ ከኢየሱስ ጋራ የመጡት ሴቶችም ተከትለው መቃብሩን አዩ፤ ሥጋውንም እንዴት እንዳስቀመጡት ተመለከቱ። ከዚያም ተመልሰው ሽቱና ቅባት አዘጋጁ፤ ሕጉ በሚያዝዘው መሠረት በሰንበት ቀን ዐረፉ።