ሉቃስ 22:54-62

ሉቃስ 22:54-62 NASV

ከዚህ በኋላ ኢየሱስን ይዘው ወሰዱት፤ ወደ ሊቀ ካህናቱም ግቢ አስገቡት፤ ጴጥሮስም በርቀት ይከተለው ነበር። ሰዎቹ በሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ እሳት አንድደው በአንድነት ተቀምጠው ሳለ፣ ጴጥሮስም ከእነርሱ ጋራ ተቀምጦ ነበር። አንዲት የቤት ሠራተኛም ጴጥሮስ እሳቱ አጠገብ ተቀምጦ አየችውና ትኵር ብላ በመመልከት፣ “ይህ ሰው ደግሞ ከርሱ ጋራ ነበረ” አለች። እርሱ ግን፣ “አንቺ ሴት፤ እኔ ዐላውቀውም” ብሎ ካደ። ከጥቂት ጊዜ በኋላም አንድ ሌላ ሰው አይቶት፣ “አንተም ደግሞ ከእነርሱ አንዱ ነህ” አለው። ጴጥሮስ ግን፣ “አንተ ሰው፤ እኔ አይደለሁም” አለ። አንድ ሰዓት ያህል ቈይቶም፣ ሌላ ሰው በርግጠኛነት፣ “ይህ ሰው የገሊላ ሰው ስለ ሆነ በእውነት ከርሱ ጋራ ነበረ” አለ። ጴጥሮስ ግን፣ “አንተ ሰው፤ የምትለውን እኔ አላውቅም” አለ፤ ይህንም ተናግሮ ገና ሳይጨርስ ዶሮ ጮኸ። ጌታም መለስ ብሎ ጴጥሮስን ተመለከተው፤ ጴጥሮስም፣ “ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ብሎ ጌታ የተናገረው ቃል ትዝ አለው። ጴጥሮስም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።