ሉቃስ 20:19-26

ሉቃስ 20:19-26 NASV

ጸሐፍትና የካህናት አለቆችም ይህን ምሳሌ የተናገረው በእነርሱ ላይ መሆኑን ስላወቁ፣ በዚያ ሰዓት ሊይዙት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ። ኢየሱስን አሳልፈው ለገዢው ኀይልና ሥልጣን ለመስጠት፣ ከአፉ በሚወጣ ቃል ለማጥመድ ይከታተሉት ነበር፤ ስለዚህም ጻድቃን መስለው የሚቀርቡ ሰላዮችን ላኩበት። ሰላዮቹም እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “መምህር ሆይ፤ አንተ ትክክለኛውን ነገር እንደምትናገርና እንደምታስተምር እንዲሁም የእግዚአብሔርን መንገድ በእውነት እንደምታስተምርና ለማንም እንደማታደላ እናውቃለን። ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?” እርሱ ግን ተንኰላቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እስኪ አንድ ዲናር አሳዩኝ፤ በላዩ ያለው የማን መልክና ጽሕፈት ነው?” እነርሱም፣ “የቄሳር ነው” ብለው መለሱለት። እርሱም፣ “እንግዲያውስ የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው። ስለዚህ በተናገረው ቃል በሕዝቡ ፊት ሊያጠምዱት አልቻሉም፤ በመልሱም ተገርመው ዝም አሉ።