ሉቃስ 20:1-47

ሉቃስ 20:1-47 NASV

አንድ ቀን ኢየሱስ ሕዝቡን በቤተ መቅደስ ሲያስተምርና ወንጌልን ሲሰብክ የካህናት አለቆች፣ ጸሐፍትና ሽማግሌዎች ተሰብስበው ወደ እርሱ መጡ። እነርሱም፣ “እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን እንደ ሆነ ንገረን፤ ሥልጣንስ የሰጠህ ማን ነው?” ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እኔም አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፤ እስኪ መልሱልኝ፤ የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበር ወይስ ከሰው?” እነርሱም እንዲህ ብለው እርስ በርስ ተመካከሩ፤ “ ‘ከሰማይ’ ብንል፣ ‘ታዲያ፣ ለምን አላመናችሁበትም?’ ይለናል፤ ‘ከሰው’ ብንል ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስ ነቢይ መሆኑን ስለሚያምኑ በድንጋይ ይወግሩናል።” ስለዚህ፣ “ከየት እንደ ሆነ አናውቅም” ብለው መለሱለት። ኢየሱስም፣ “እንግዲያውስ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ለሕዝቡ ይነግራቸው ጀመር፤ “አንድ ሰው የወይን ተክል ተከለ፤ ለገበሬዎችም አከራየና ወደ ሌላ አገር ሄዶ ብዙ ጊዜ ቈየ። በመከርም ወራት፣ ከወይኑ ፍሬ እንዲልኩለት ባሪያውን ወደ ገበሬዎቹ ላከ፤ ገበሬዎቹ ግን ባሪያውን ደብድበው ባዶ እጁን ሰደዱት። ቀጥሎም ሌላ ባሪያውን ላከ፤ ገበሬዎቹም እርሱንም ደግሞ ደበደቡት፤ አዋርደውም ባዶ እጁን ሰደዱት። አሁንም ቀጥሎ ሦስተኛ አገልጋዩን ላከ፤ ገበሬዎቹም እርሱንም ደግሞ አቍስለው ወደ ውጭ ጣሉት። “የወይኑ ተክል ባለቤትም፣ ‘እንግዲህ ምን ላድርግ? እስኪ ደግሞ የምወድደውን ልጄን እልካለሁ፤ ምናልባት እርሱን ያከብሩት ይሆናል’ አለ። “ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩት ጊዜ፣ ‘ይህ እኮ ወራሹ ነው፣ ኑና እንግደለው፤ በዚህም ርስቱ የእኛ ይሆናል’ እየተባባሉ ተመካከሩ፤ ከወይኑም ተክል ቦታ ወደ ውጭ አውጥተው ገደሉት። “እንግዲህ የወይኑ ተክል ባለቤት ምን ያደርጋቸዋል? መጥቶ እነዚያን ገበሬዎች ያጠፋቸዋል፤ የወይኑንም ተክል ቦታ ለሌሎች ይሰጣል።” ሕዝቡም ይህን በሰሙ ጊዜ፣ “እንዲህ ያለውንስ አያምጣው” አሉ። ኢየሱስም ወደ እነርሱ ተመልክቶ እንዲህ አላቸው፤ “ ‘ታዲያ ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ’ ተብሎ የተጻፈው ትርጕሙ ምንድን ነው? በዚህ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ሁሉ ይቀጠቀጣል፤ ድንጋዩም በላዩ የሚወድቅበት ሁሉ ይደቅቃል።” ጸሐፍትና የካህናት አለቆችም ይህን ምሳሌ የተናገረው በእነርሱ ላይ መሆኑን ስላወቁ፣ በዚያ ሰዓት ሊይዙት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ። ኢየሱስን አሳልፈው ለገዢው ኀይልና ሥልጣን ለመስጠት፣ ከአፉ በሚወጣ ቃል ለማጥመድ ይከታተሉት ነበር፤ ስለዚህም ጻድቃን መስለው የሚቀርቡ ሰላዮችን ላኩበት። ሰላዮቹም እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “መምህር ሆይ፤ አንተ ትክክለኛውን ነገር እንደምትናገርና እንደምታስተምር እንዲሁም የእግዚአብሔርን መንገድ በእውነት እንደምታስተምርና ለማንም እንደማታደላ እናውቃለን። ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?” እርሱ ግን ተንኰላቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እስኪ አንድ ዲናር አሳዩኝ፤ በላዩ ያለው የማን መልክና ጽሕፈት ነው?” እነርሱም፣ “የቄሳር ነው” ብለው መለሱለት። እርሱም፣ “እንግዲያውስ የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው። ስለዚህ በተናገረው ቃል በሕዝቡ ፊት ሊያጠምዱት አልቻሉም፤ በመልሱም ተገርመው ዝም አሉ። ትንሣኤ የለም ከሚሉት ሰዱቃውያን አንዳንዶቹ ወደ ኢየሱስ መጥተው ጥያቄ አቀረቡለት፤ እንዲህም አሉት፤ “መምህር ሆይ፤ አንድ ሰው ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፣ ወንድሙ የሟችን ሚስት አግብቶ ልጆች በመውለድ ለወንድሙ ዘር እንዲተካ ሙሴ ጽፎልናል። ታዲያ፣ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ የመጀመሪያው ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤ ሁለተኛውም እንደዚሁ፤ ሦስተኛው ደግሞ አገባት፤ ሰባቱም እንዲሁ እያሉ አግብተዋት ልጆች ሳይወልዱ ሞቱ። በመጨረሻም ሴትዮዋ ሞተች። እንግዲህ ሰባቱም ስላገቧት፣ በትንሣኤ ጊዜ የማን ሚስት ትሆናለች?” ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የዚህ ዓለም ልጆች ያገባሉ፤ ይጋባሉም፤ የሚመጣውን ዓለምና የሙታንን ትንሣኤ ማግኘት የሚገባቸው ግን አያገቡም፤ አይጋቡም፤ እንደ መላእክትም ስለሚሆኑ ከዚያ በኋላ አይሞቱም፤ የትንሣኤ ልጆች ስለ ሆኑም የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው። ሙሴ ስለ ቍጥቋጦ በተጻፈው ታሪክ ውስጥ ጌታን፣ ‘የአብርሃም አምላክ፣ የይሥሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ’ በማለቱ ሙታን እንደሚነሡ ያሳያል፤ ሁሉም ለርሱ ሕያዋን ስለ ሆኑ፣ እርሱ የሕያዋን አምላክ እንጂ የሙታን አይደለም።” አንዳንድ ጸሐፍትም፣ “መምህር ሆይ፤ መልካም ተናገርህ” አሉት። ከዚህ በኋላ አንድ ሰው እንኳ ሊጠይቀው አልደፈረም። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “ሰዎች ክርስቶስን እንዴት የዳዊት ልጅ ነው ይሉታል? ምክንያቱም ራሱ ዳዊት በመዝሙር መጽሐፉ እንዲህ ብሏል፤ “ ‘ጌታ ጌታዬን፣ “በቀኜ ተቀመጥ፤ ጠላቶችህን፣ ለእግርህ መረገጫ እስከማደርግልህ ድረስ።” ’ እንግዲህ ዳዊት እርሱን፣ ‘ጌታ’ ብሎ ሲጠራው እንዴት ልጁ ይሆናል?” ሕዝቡ ሁሉ እየሰሙትም ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፤ ከጸሐፍት ተጠንቀቁ፤ “ዘርፋፋ ቀሚስ ለብሰው መዞርን፣ በገበያ ስፍራ የአክብሮት ሰላምታን፣ በምኵራብ የከበሬታ መቀመጫን፣ በግብዣ ቦታም የክብር ስፍራን ይፈልጋሉና፤ በረዥም ጸሎታቸው እያሳበቡ የመበለቶችን ቤት ያራቍታሉ፤ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ።”