ሉቃስ 19:19-31

ሉቃስ 19:19-31 NASV

“ጌታውም፣ ‘አንተ ደግሞ በዐምስት ከተሞች ላይ ሥልጣን ተሰጥቶሃል’ አለው። “ሌላውም አገልጋይ ቀርቦ እንዲህ አለው፤ ‘ጌታ ሆይ፤ በጨርቅ ጠቅልዬ ያቈየሁት ምናንህ ይኸው፤ አንተ ያላስቀመጥኸውን የምትወስድ፣ ያልዘራኸውን የምታጭድ ጨካኝ ሰው ስለ ሆንህ ፈራሁህ።’ “ጌታውም እንዲህ አለው፤ ‘አንተ ክፉ ባሪያ! በራስህ ቃል እፈርድብሃለሁ፤ ያላስቀመጥሁትን የምወስድ፣ ያልዘራሁትን የማጭድ፣ ጨካኝ ሰው መሆኔን ካወቅህ፣ መጥቼ ገንዘቤን ከነትርፉ እንድወስድ፣ ለምን ለሚሠሩበት ሰዎች አልሰጠህም?’ “ጌታውም እዚያ የቆሙትን፣ ‘ምናኑን ውሰዱበትና ዐሥር ምናን ላለው ስጡት’ አላቸው። “እነርሱም፣ ‘ጌታ ሆይ፤ እርሱ እኮ ዐሥር ምናን አለው’ አሉት። “እርሱም እንዲህ አለ፤ ‘እላችኋለሁ፤ ላለው ይጨመርለታል፤ የሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። ነገር ግን እኔ በላያቸው እንዳልነግሥ የፈለጉትን እነዚያን ጠላቶቼን ወደዚህ አምጡና በፊቴ ዕረዷቸው።’ ” ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ሊወጣ ቀድሟቸው ይሄድ ነበር። ደብረ ዘይት በተባለው ተራራ ወደሚገኙት፣ ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ ከተሞች በቀረበ ጊዜ፣ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፤ ወደዚያም ስትገቡ ሰው ተቀምጦበት የማያውቅ የአህያ ውርንጫ እዚያ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ ወደዚህ አምጡት። ማንም፣ ‘ለምን ትፈቱታላችሁ?’ ብሎ ቢጠይቃችሁ፣ ‘ለጌታ ያስፈልገዋል’ በሉት።”