ሉቃስ 13:22-30

ሉቃስ 13:22-30 NASV

ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እያመራ ሳለ፣ በሚያልፍባቸው ከተሞችና መንደሮች እያስተማረ ያልፍ ነበር። አንድ ሰውም ቀርቦ፣ “ጌታ ሆይ፤ የሚድኑት ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸውን?” አለው። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “በጠባቡ በር ለመግባት ተጣጣሩ፤ እላችኋለሁ፤ ብዙዎች ለመግባት ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን አይችሉም። የቤቱ ባለቤት ተነሥቶ በሩን ከቈለፈ በኋላ በውጭ ቆማችሁ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ በሩን ክፈትልን’ እያላችሁ በሩን ማንኳኳት ትጀምራላችሁ። “እርሱ ግን፣ ‘ማን እንደ ሆናችሁና ከየት እንደ መጣችሁ አላውቅም’ ብሎ ይመልስላችኋል። “እናንተም፣ ‘ከአንተ ጋራ ዐብረን በልተናል፤ ጠጥተናል፤ በአደባባያችንም አስተምረሃል’ ትላላችሁ። “እርሱም፣ ‘እላችኋለሁ፤ አላውቃችሁም ከየት እንደ መጣችሁም አላውቅም፤ እናንተ ዐመፀኞች ሁሉ ከእኔ ራቁ’ ይላል። “አብርሃምን፣ ይሥሐቅንና ያዕቆብን፣ ነቢያትንም ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ስታዩ፣ እናንተ ግን ወደ ውጭ ተጥላችሁ ስትቀሩ፣ በዚያ ጊዜ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። ሰዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ፣ ከሰሜንና ከደቡብ መጥተው በእግዚአብሔር መንግሥት በማእድ ይቀመጣሉ። እነሆ፤ ከኋለኞች መካከል ፊተኞች የሚሆኑ፣ ከፊተኞች መካከልም ኋለኞች የሚሆኑ አሉ።”