በዚያ ጊዜ፣ በብዙ ሺሕ የሚቈጠር ሕዝብ እርስ በርስ እስኪረጋገጥ ድረስ ተሰብስቦ ሳለ፣ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ይል ጀመር፤ “ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠንቀቁ፤ ይህም ግብዝነት ነው። የማይገለጥ የተሸፈነ፣ የማይታወቅ የተሰወረ ምንም የለም። ስለዚህ በጨለማ ያወራችሁት ሁሉ በብርሃን ይሰማል፤ በእልፍኝም ውስጥ በጆሮ ያንሾካሾካችሁት በሰገነት በይፋ ይነገራል። “ወዳጆቼ ሆይ፤ እላችኋለሁ፣ ሥጋን የሚገድሉትን፣ ከዚያ ወዲያ ግን ምንም ማድረግ የማይችሉትን አትፍሩ። ነገር ግን መፍራት የሚገባችሁን አሳያችኋለሁ፤ ከገደለ በኋላ ወደ ገሃነም ለመጣል ሥልጣን ያለውን እርሱን ፍሩት፤ አዎን፣ እርሱን ፍሩት እላችኋለሁ። ዐምስት ድንቢጦች በዐሥር ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ይሁን እንጂ ከእነርሱ አንዲቷ እንኳ በእግዚአብሔር ዘንድ አትዘነጋም። የእናንተ የራሳችሁ ጠጕር ሁሉ እንኳ የተቈጠረ ነው፤ እንግዲህ አትፍሩ፤ ከብዙ ድንቢጦች የበለጠ ዋጋ አላችሁ። “እላችኋለሁ፤ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ፣ የሰው ልጅ ደግሞ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይመሰክርለታል። በሰው ፊት የሚክደኝም በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይካዳል። በሰው ልጅ ላይ የማቃለል ቃል የሚሰነዝር ሁሉ ይሰረይለታል፤ መንፈስ ቅዱስን የሚሳደብ ግን አይሰረይለትም። “ሰዎች ይዘው ወደ ምኵራብ፣ ወደ ገዥዎችና ወደ ባለሥልጣናት በሚያቀርቧችሁ ጊዜ ሁሉ፣ እንዴት ወይም ምን እንደምትመልሱ አትጨነቁ፤ በዚያ ሰዓት መንፈስ ቅዱስ መናገር የሚገባችሁን ያስተምራችኋልና።” ከሕዝቡም መካከል አንድ ሰው፣ “መምህር ሆይ፤ ወንድሜ ውርስ እንዲያካፍለኝ ንገረው” አለው። ኢየሱስም፣ “አንተ ሰው፤ በእናንተ ላይ ፈራጅ ወይም ዳኛ ያደረገኝ ማነው?” አለው። ደግሞም፣ “የሰው ሕይወቱ በሀብቱ ብዛት የተመሠረተ ስላልሆነ ተጠንቀቁ፤ ከስግብግብነትም ሁሉ ራሳችሁንም ጠብቁ” አላቸው። ቀጥሎም እንዲህ ሲል ምሳሌ ነገራቸው፤ “ዕርሻው እጅግ ፍሬያማ የሆነችለት አንድ ሀብታም ነበረ፤ ይህም ሰው፣ ‘ምርቴን የማከማችበት ስፍራ ስለሌለኝ ምን ላድርግ?’ ብሎ በልቡ ዐሰበ። “እንዲህም አለ፤ ‘እንደዚህ አደርጋለሁ፤ ያሉኝን ጐተራዎች አፈርስና ሌሎች ሰፋ ያሉ ጐተራዎች እሠራለሁ፤ በዚያም ምርቴንና ንብረቴንም ሁሉ አከማቻለሁ፤ ነፍሴንም፣ “ነፍሴ ሆይ፤ ለብዙ ዘመን የሚበቃሽ ሀብት አከማችቼልሻለሁ፤ እንግዲህ ዕረፊ፤ ብዪ፤ ጠጪ፤ ደስም ይበልሽ” እላታለሁ።’ “እግዚአብሔር ግን፣ ‘አንተ ሞኝ፤ ነፍስህን በዚህች ሌሊት ከአንተ ሊወስዱ ይፈልጓታል፤ እንግዲህ፣ ለራስህ ያከማቸኸው ለማን ይሆናል?’ አለው። “ስለዚህ ለራሱ ሀብት የሚያከማች፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ሀብታም ያልሆነ ሰው መጨረሻው ይኸው ነው።” ከዚያም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፤ “ስለዚህ እላችኋለሁ፣ ስለ ሕይወታችሁ ምን እንደምትበሉ ወይም ስለ ሰውነታችሁ ምን እንደምትለብሱ አትጨነቁ፤ ሕይወት ከምግብ፣ ሰውነትም ከልብስ ይበልጣልና። ቍራዎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱም፤ ማከማቻ ወይም ጐተራ የላቸውም፤ እግዚአብሔር ግን ይመግባቸዋል። እናንተማ ከወፎች እጅግ ትበልጡ የለምን? ለመሆኑ፣ ከእናንተ ተጨንቆ በዕድሜው ላይ አንድ ሰዓት መጨመር የሚችል ማን ነው? እንግዲህ ቀላሉን ነገር እንኳ ማድረግ የማትችሉ ከሆነ፣ ስለ ሌላው ነገር ለምን ትጨነቃላችሁ? “እስኪ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ ተመልከቱ፤ አይለፉም፤ አይፈትሉም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰሎሞን እንኳ በዚያ ሁሉ ክብሩ ከእነርሱ እንደ አንዷ አልለበሰም። እናንተ እምነት የጐደላችሁ፤ እንግዲህ እግዚአብሔር ዛሬ ታይቶ ነገ ወደ እሳት የሚጣለውን የሜዳ ሣር እንዲህ የሚያለብስ ከሆነ፣ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁ? ስለዚህ ምን እንደምትበሉና ምን እንደምትጠጡ አትሹ፤ አትጨነቁም፤ ይህንማ በዓለም ያሉ ሰዎች ሁሉ አጥብቀው ይሻሉ፤ አባታችሁም እነዚህ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል። ይልቁንስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ፈልጉ፤ እነዚህም ይጨመሩላችኋል። “እናንተ አነስተኛ መንጋ የሆናችሁ፤ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ መልካም ፈቃድ ነውና አትፍሩ፤ ያላችሁን ሽጡና ለድኾች ስጡ፤ ሌባ በማይሰርቅበት፣ ብል በማይበላበት፣ በማያረጅ ከረጢት የማያልቅ ሀብት በሰማይ አከማቹ፤ ሀብታችሁ ባለበት ልባችሁ በዚያ ይሆናልና። “በዐጭር ታጥቃችሁ ተዘጋጁ፤ መብራታችሁም የበራ ይሁን፤ ጌታቸው ከሰርግ ግብዣ እስኪመለስ የሚጠባበቁና መጥቶም በር ሲያንኳኳ ወዲያው ለመክፈት ዝግጁ የሆኑ ሰዎችን ምሰሉ። ጌታቸው በሚመጣበት ጊዜ ነቅተው የሚያገኛቸው ባሮች ብፁዓን ናቸው። እውነት እላችኋለሁ፤ ጌታቸውም በዐጭር ይታጠቃል፤ በማእድ ያስቀምጣቸዋል፤ ቀርቦም ያስተናግዳቸዋል። ከሌሊቱ በሁለተኛውም ሆነ በሦስተኛው ክፍል መጥቶ እንደዚያው ነቅተው ቢያገኛቸው፣ እነዚያ ባሮች ብፁዓን ናቸው። ይህን ግን ዕወቁ፤ ሌባ በምን ሰዓት እንደሚመጣ ባለቤቱ ቢያውቅ ኖሮ፣ ቤቱ ሲቈፈር ዝም ብሎ ባላየ ነበር። የሰው ልጅም ባላሰባችሁት ሰዓት ይመጣል፤ እናንተም እንደዚሁ ዝግጁ ሁኑ።” ጴጥሮስም፣ “ጌታ ሆይ፤ ይህን ምሳሌ የምትናገረው ለእኛ ብቻ ነው ወይስ ለሁሉም ጭምር ነው?” አለው። ጌታም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እንግዲህ፣ ምግባቸውን በተገቢው ጊዜ እንዲሰጣቸው፣ ጌታው በቤተ ሰዎቹ ላይ የሚሾመው ታማኝና ብልኅ መጋቢ ማነው? ጌታው ሲመለስ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ባሪያ እርሱ ምስጉን ነው። እውነት እላችኋለሁ፤ ባለው ንብረት ሁሉ ላይ ይሾመዋል። ነገር ግን ያ ባሪያ፣ ‘ጌታዬ ቶሎ አይመጣም፤ ይዘገያል’ ብሎ ቢያስብና ወንድና ሴት ብላቴኖችን ቢደበድብ፣ ደግሞም እንዳሻው ቢበላና ቢጠጣ መስከር ቢጀምር፣ የዚያ ባሪያ ጌታ ባላሰበው ቀንና ባልጠረጠረው ሰዓት ይመጣበታል፤ ስለዚህ ይቈራርጠዋል፤ ዕድል ፈንታውንም ከማያምኑ ጋራ ያደርጋል። “የጌታውን ፍላጎት እያወቀ የማይዘጋጅና ፈቃዱን የማያደርግ ባሪያ እርሱ ክፉኛ ይገረፋል፤ ነገር ግን ይህን ሳያውቅ ቀርቶ መገረፍ የሚገባውን ያህል ያደረገ አገልጋይ በጥቂቱ ይገረፋል። ብዙ ከተሰጠው ሁሉ ብዙ ይፈለግበታል፤ ብዙ ዐደራ ከተቀበለም ብዙ ይጠበቅበታል። “እኔ የመጣሁት በምድር ላይ እሳት ለመለኰስ ነው፤ አሁኑኑ ቢቀጣጠል ምንኛ ደስ ባለኝ! ነገር ግን የምጠመቀው ጥምቀት አለኝ፤ እስኪፈጸምም ድረስ እንዴት ተጨንቄአለሁ? በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ ይመስላችኋል? አይደለም፤ እላችኋለሁ፤ እኔ የመጣሁት ለመለያየት ነው። ከአሁን ጀምሮ እርስ በርስ የተለያዩ በአንድ ቤተ ሰብ ውስጥ ዐምስት ሰዎች ይኖራሉ፤ ሁለቱ በሦስቱ ላይ፣ ሦስቱም በሁለቱ ላይ ተነሥተው ይለያያሉ። አባት በወንድ ልጁ ላይ፣ ወንድ ልጅም በአባቱ ላይ፣ እናት በሴት ልጇ ላይ፣ ሴት ልጅም በእናቷ ላይ፣ ዐማት በምራቷ ላይ፣ ምራትም በዐማቷ ላይ ተነሥተው ይለያያሉ።” ደግሞም ለሕዝቡ እንዲህ አለ፤ “ደመና በምዕራብ በኩል ሲወጣ ስታዩ ወዲያው፣ ‘ዝናብ ሊመጣ ነው’ ትላላችሁ፤ እንደዚያም ይሆናል፤ የደቡብ ነፋስም ከደቡብ በኩል ሲነፍስ፣ ‘ቀኑ ሞቃት ይሆናል’ ትላላችሁ፤ እንደዚያም ይሆናል። እናንተ ግብዞች፤ የምድሩንና የሰማዩን መልክ መመርመር ታውቁበታላችሁ፤ ታዲያ ይህን የአሁኑን ዘመን መመርመር እንዴት ተሳናችሁ? “ታዲያ ራሳችሁ ትክክለኛ የሆነውን ነገር ለምን አትፈርዱም? ከባላጋራህ ጋራ ወደ ዳኛ ፊት ለመቅረብ ስትሄድ፣ ገና በመንገድ ላይ ሳለህ ለመታረቅ ጥረት አድርግ፤ አለዚያ ጐትቶ ወደ ዳኛው ይወስድሃል፤ ዳኛውም ለመኰንኑ አሳልፎ ይሰጥሃል፤ መኰንኑም ወደ ወህኒ ይጥልሃል። እልሃለሁ፤ የመጨረሻዋን ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከዚያ አትወጣም።”
ሉቃስ 12 ያንብቡ
ያዳምጡ ሉቃስ 12
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሉቃስ 12:1-59
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች