ሉቃስ 1:26-55

ሉቃስ 1:26-55 NASV

በስድስተኛው ወር፣ እግዚአብሔር መልአኩ ገብርኤልን በገሊላ ወደምትገኘው ናዝሬት ወደምትባል ከተማ ላከው፤ የተላከውም ከዳዊት ዘር ለሆነ ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ነበር፤ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ። መልአኩም እርሷ ወዳለችበት ገብቶ፣ “እጅግ የተወደድሽ ሆይ! ሰላም ለአንቺ ይሁን፤ ጌታ ከአንቺ ጋራ ነው፤ አንቺ የተባረክሽ ነሽ” አላት። ማርያምም በንግግሩ እጅግ በጣም ደንግጣ፣ “ይህ ምን ዐይነት ሰላምታ ይሆን?” እያለች ነገሩን ታሰላስል ጀመር፤ መልአኩም እንዲህ አላት፤ “ማርያም ሆይ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆ፤ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱም ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብም ቤት ላይ ለዘላለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።” ማርያምም መልአኩን፣ “እኔ ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” አለችው። መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፤ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑልም ኀይል ይጸልልሻል፤ ስለዚህ የሚወለደው ቅዱሱ ሕፃን፣ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል። እነሆ፤ ዘመድሽ ኤልሳቤጥም በስተ እርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፤ መካን የተባለችውም ስድስተኛ ወሯን ይዛለች፤ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና።” ማርያምም፣ “እነሆ፤ እኔ የጌታ ባሪያ ነኝ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” አለች። ከዚያም መልአኩ ተለይቷት ሄደ። ማርያምም በዚያው ሰሞን በፍጥነት ተነሥታ ወደ ደጋው አገር፣ ወደ አንድ የይሁዳ ከተማ ሄደች፤ ወደ ዘካርያስ ቤትም ገብታ ለኤልሳቤጥ ሰላምታ አቀረበች። ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ፣ ፅንሱ በማሕፀኗ ውስጥ ዘለለ፤ ኤልሳቤጥም በመንፈስ ቅዱስ ተሞላች፤ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች፤ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማሕፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። ለመሆኑ የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እኔ ማን ነኝ? እነሆ፤ የሰላምታሽ ድምፅ ጆሮዬ እንደ ገባ፣ በማሕፀኔ ያለው ፅንስ በደስታ ዘሏልና። ጌታ ይፈጸማል ብሎ የነገራትን ያመነች እርሷ ብፅዕት ናት!” ማርያምም እንዲህ አለች፤ “ነፍሴ ጌታን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፤ መንፈሴም በመድኀኒቴ በእግዚአብሔር ደስ ትሠኛለች፤ እርሱ የባሪያውን መዋረድ ተመልክቷልና። ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ምስጉን ይሉኛል፤ ኀያል የሆነው እርሱ ታላቅ ነገር አድርጎልኛልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው፤ ምሕረቱም ለሚፈሩት ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል። በክንዱ ብርቱ ሥራ ሠርቷል፤ በልባቸው ሐሳብ የሚታበዩትን በትኗቸዋል፤ ገዦችን ከዙፋናቸው አውርዷቸዋል፤ ትሑታንን ግን ከፍ ከፍ አድርጓቸዋል፤ የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቧቸዋል፤ ሀብታሞችን ግን ባዷቸውን ሰድዷቸዋል፤ ምሕረቱን በማስታወስ፣ ብላቴናውን እስራኤልን ረድቷል፤ ይህም ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ፣ ለአብርሃምና ለዘሩ ያለውን ለዘላለም ለመጠበቅ ነው።”