ዘሌዋውያን 7:28-38

ዘሌዋውያን 7:28-38 NASV

እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፤ ‘የኅብረት መሥዋዕት ለእግዚአብሔር የሚያቀርብ ማንኛውም ሰው ስለ ራሱ መሥዋዕት አድርጎ ከዚሁ ላይ ለእግዚአብሔር ያቅርብ። በእሳት ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን መሥዋዕት በራሱ እጅ ያቅርበው፤ ሥቡን ከፍርምባው ጋራ ያቅርብ፤ ፍርምባውን መሥዋዕት አድርጎ በእግዚአብሔር ፊት ይወዝውዘው። ካህኑ ሥቡን በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ ፍርምባው ግን ለአሮንና ለልጆቹ ይሰጥ። የኅብረት መሥዋዕታችሁን የቀኝ ወርች ለካህኑ የተለየ አድርጋችሁ ስጡት። የኅብረት መሥዋዕቱን ደምና ሥብ የሚያቀርበው የአሮን ልጅ ቀኝ ወርቹን የራሱ ድርሻ አድርጎ ይውሰድ። ከእስራኤላውያን የኅብረት መሥዋዕት ላይ የተወዘወዘውን ፍርምባና የቀረበውን ወርች ወስጃለሁ፤ ለካህኑ ለአሮንና ለልጆቹም ከእስራኤላውያን የሚያገኙት መደበኛ ድርሻቸው እንዲሆን ሰጥቻቸዋለሁ።’ ” ካህናት ሆነው እግዚአብሔርን እንዲያገለግሉ በቀረቡ ቀን፣ በእሳት ለእግዚአብሔር ከቀረበው መሥዋዕት ላይ ለአሮንና ለልጆቹ የተመደበላቸው ድርሻ ይህ ነው። ካህናቱ በተቀቡበት ቀን፣ እስራኤላውያን መደበኛ ድርሻ አድርገው ከትውልድ እስከ ትውልድ ይህን እንዲሰጧቸው እግዚአብሔር አዘዘ። እንግዲህ የሚቃጠል መሥዋዕት፣ የእህል ቍርባን፣ የኀጢአት መሥዋዕት፣ የበደል መሥዋዕት፣ የክህነት ሹመት መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት ሥርዐት ይህ ነው፤ ይህም፣ በሲና ምድረ በዳ እስራኤላውያን መሥዋዕታቸውን ለእግዚአብሔር እንዲያቀርቡ ባዘዛቸው ቀን በሲና ተራራ ላይ ለሙሴ የሰጠው ሥርዐት ነው።