ዘሌዋውያን 6:14-23

ዘሌዋውያን 6:14-23 NASV

“ ‘የእህል ቍርባን ሥርዐት ይህ ነው፦ የአሮን ልጆች ቍርባኑን በመሠዊያው ትይዩ በእግዚአብሔር ፊት ያቅርቡት። ካህኑ ከላመው ዱቄትና ከዘይቱ አንድ ዕፍኝ ያንሣለት፤ በእህሉ ቍርባን ላይ ያለውንም ዕጣን በሙሉ ይውሰድ፤ ይህንም፣ ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ፣ ለመታሰቢያ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው። የተረፈውንም አሮንና ልጆቹ ይብሉት፤ ቂጣውን በተቀደሰው ስፍራ፣ በመገናኛው ድንኳን ቅጥር ግቢ ውስጥ አደባባዩ ላይ ይብሉት። ያለ እርሾ መጋገር አለበት፤ በእሳት ከሚቀርብልኝ ቍርባን ይህን የእነርሱ ድርሻ አድርጌ ሰጥቻቸዋለሁ። ይህም፣ እንደ ኀጢአት መሥዋዕትና እንደ በደል መሥዋዕት ሁሉ እጅግ የተቀደሰ ነው። ማንኛውም ከአሮን ዘር የተወለደ ወንድ ሊበላው ይችላል፤ ለእግዚአብሔር ከሚቀርበው የእሳት ቍርባን ለርሱ የተመደበ የዘላለም ድርሻው ነው፤ የሚነካውም ሁሉ ቅዱስ ይሆናል።’ ” እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “አሮን ወይም ልጆቹ በተቀቡበት ዕለት ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት ቍርባን ይህ ነው፦ የኢፍ አንድ ዐሥረኛው የላመ ዱቄት ግማሹን ለጧት፣ ግማሹን ለማታ የዘወትር የእህል ቍርባን አድርገው ያቅርቡት። በሚገባ በዘይት ተለውሶ በምጣድ ላይ ይጋገር፤ ከዚያም የእህሉን ቍርባን ቈራርሰህ ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆን ዘንድ አቅርብ። በርሱ ቦታ ተቀብቶ ካህን የሚሆነው ልጁ ይህን ያዘጋጅ፤ ለእግዚአብሔር የተመደበ ድርሻ ነውና ፈጽሞ ይቃጠል። ካህኑ የሚያቀርበው የእህል ቍርባን ሁሉ ፈጽሞ ይቃጠል እንጂ አይበላ።”