ዘሌዋውያን 5:7-13

ዘሌዋውያን 5:7-13 NASV

“ ‘ሰውየው ስለ ሠራው ኀጢአት በግ ለማቅረብ ዐቅሙ ካልፈቀደ ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የዋኖስ ጫጩቶች የመጀመሪያውን ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ሁለተኛውን ለሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ያቅርብ። ወደ ካህኑም ያምጣቸው፤ እርሱም ለኀጢአት መሥዋዕት የምትሆነውን አስቀድሞ ያቅርብ፤ ራሷን ዐንገቷ ላይ ይቈልምም፤ ነገር ግን ቈርጦ አይጣል፤ ከኀጢአት መሥዋዕቱም ጥቂት ደም ወስዶ በመሠዊያው ዙሪያ ላይ ይርጨው፤ የተረፈውም ደም ሁሉ በመሠዊያው ግርጌ ይፍሰስ፤ ይህም የኀጢአት መሥዋዕት ነው። ካህኑም ቀደም ሲል በታዘዘው መሠረት ሁለተኛዋን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ፤ ካህኑም የሰውየውን ኀጢአት ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ይቅር ይባላል። “ ‘ሰውየው ሁለት ርግቦች ወይም ሁለት የዋኖስ ጫጩቶች ለማቅረብ ዐቅሙ ካልፈቀደ፣ ስለ ሠራው ኀጢአት የኢፍ መስፈሪያ አንድ ዐሥረኛ የላመ ዱቄት ለኀጢአት መሥዋዕት ያቅርብ፤ ነገር ግን የኀጢአት መሥዋዕት ስለ ሆነ ዘይት አያፍስስበት፤ ዕጣንም አይጨምርበት፤ ከዚያም ለካህኑ ያቅርብ፤ ካህኑም ለመታሰቢያ እንዲሆን ዕፍኝ ሙሉ ይዝገንለት፤ በእሳት ከሚቀርበውም ቍርባን በላይ አድርጎ ለእግዚአብሔር በመሠዊያው ላይ በእሳት ያቃጥለው፤ ይህም የኀጢአት መሥዋዕት ነው። ሰውየው ከእነዚህ በአንዱ ኀጢአት ቢሠራ፣ ካህኑ በዚህ ሁኔታ ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ይቅር ይባላል። ከመሥዋዕቱ የተረፈውም እንደ እህል ቍርባን ሁሉ ለካህኑ ይሆናል።’ ”