እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘ማንኛውም ሰው ተመጣጣኙን ዋጋ በመክፈል ለእግዚአብሔር ሰውን ለመስጠት የተለየ ስእለት ቢሳል፣ ዕድሜው ከሃያ እስከ ስድሳ ዓመት ለሆነ ወንድ፣ በቤተ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መሠረት፣ ግምቱ ዐምሳ ጥሬ ሰቅል ብር ይሁን። ለሴት ከሆነ ግምቱ ሠላሳ ሰቅል ይሁን። ዕድሜው ከዐምስት እስከ ሃያ ዓመት ለሆነ ሰው፣ ወንድ ከሆነ ግምቱ ሃያ ሰቅል፣ ሴት ከሆነች ግምቷ ዐሥር ሰቅል ይሁን። ዕድሜው ከአንድ ወር እስከ ዐምስት ዓመት ለሆነ ሰው፣ ወንድ ከሆነ ግምቱ ዐምስት ሰቅል ጥሬ ብር፣ ለሴት ከሆነ ሦስት ሰቅል ጥሬ ብር ይሁን። ስድሳ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ ለሆነ ሰው፣ ወንድ ከሆነ ግምቱ ዐሥራ ዐምስት ሰቅል፣ ሴት ከሆነች ዐሥር ሰቅል ይሁን። ስእለት የተሳለው ድኻ ከሆነና ግምቱን መክፈል ካልቻለ ግን፣ ለስጦታ ያሰበውን ሰው ወደ ካህኑ ያምጣ፤ ካህኑም የተሳለው ሰው ባለው ዐቅም መሠረት መክፈል የሚገባውን ይተምንለታል። “ ‘ሰውየው የተሳለው ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ሆኖ መቅረብ የሚችል እንስሳ ከሆነ፣ እንዲህ ያለው ለእግዚአብሔር የተሰጠ እንስሳ የተቀደሰ ይሆናል። ሰውየው መልካም የሆነውን እንስሳ መልካም ባልሆነው፣ መልካም ያልሆነውንም መልካም በሆነው አይለውጥ ወይም አይተካ፤ አንዱን እንስሳ በሌላው ከተካም ሁለቱ የተቀደሱ ይሆናሉ። እንስሳው በሥርዐቱ መሠረት የረከሰ፣ ለእግዚአብሔርም መሥዋዕት ሆኖ መቅረብ የማይገባው ከሆነ፣ ሰውየው እንስሳውን ወደ ካህኑ ያቅርብ፤ መልካም ቢሆን ወይም ባይሆን፣ ካህኑ ዋጋውን ይወስን፤ የካህኑም ውሳኔ የጸና ይሆናል። ባለቤቱ እንስሳውን መዋጀት ከፈለገ ግን፣ በተተመነው ዋጋ ላይ አንድ ዐምስተኛ መጨመር አለበት።
ዘሌዋውያን 27 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘሌዋውያን 27
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘሌዋውያን 27:1-13
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች