ዘሌዋውያን 26:4-10

ዘሌዋውያን 26:4-10 NASV

ዝናብን በወቅቱ እሰጣችኋለሁ፤ ምድሪቱ እህሏን፣ የሜዳ ዛፎችም ፍሬአቸውን ይሰጣሉ። የምትወቁት እህል፣ የወይን ዘለላ እስከምትቈርጡበት ጊዜ፣ የምትቈርጡትም የወይን ዘለላ፣ እህል እስከምትዘሩበት ጊዜ ያደርሷችኋል፤ ምግባችሁን እስክትጠግቡ ትበላላችሁ፤ በምድራችሁም ላይ ያለ ሥጋት ትኖራላችሁ። “ ‘በምድሪቱ ላይ ሰላምን እሰጣለሁ፤ ትተኛላችሁ፤ ማንም አያስፈራችሁም። ክፉ አራዊትን ከምድሪቱ አስወግዳለሁ፤ ሰይፍም በምድራችሁ ላይ አያልፍም። ጠላቶቻችሁን ታሳድዳላችሁ፤ እነርሱም በፊታችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ። ከእናንተ ዐምስቱ መቶውን፣ መቶውም ዐሥሩን ሺሕ ያሳድዳሉ፤ ጠላቶቻችሁም በፊታችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ። “ ‘ፊቴን ወደ እናንተ እመልሳለሁ፤ እንድታፈሩና እንድትበዙም አደርጋችኋለሁ፤ ቃል ኪዳኔንም ከእናንተ ጋራ አጸናለሁ። የዓምናውን እህል እየበላችሁ ከጐተራው ሳያልቅ ለዘንድሮው እህል ደግሞ ቦታ ታስለቅቃላችሁ።