“ ‘ሰባት የሰንበት ዓመታት ማለትም ሰባት ጊዜ ሰባት ዓመታትን ቍጠር፤ ሰባቱ የሰንበት ዓመታትም አርባ ዘጠኝ ዓመታት ይሆናሉ። ከዚያም በኋላ በሰባተኛው ወር በዐሥረኛው ቀን፣ መለከት ይነፋ፤ በማስተስረያ ቀንም በምድራችሁ ሁሉ መለከት ንፉ። ዐምሳኛውን ዓመት ቀድሱ፤ በምድሪቱ ሁሉ ላሉ ነዋሪዎች በሙሉ ነጻነት ዐውጁ፤ ይህም ኢዮቤልዩ ይሁንላችሁ፤ ከእናንተ እያንዳንዱ ወደ ቤተ ሰቡ ርስት፣ ወደ ወገኑም ይመለስ። የኀምሳኛው ዓመት ኢዮቤልዩ ይሁንላችሁ፤ አትዝሩ፤ ሳትዘሩት የበቀለውን አትጨዱ፤ ካልተገረዘውም የወይን ሐረግ ፍሬ አትሰብስቡ። ኢዮቤልዩ ስለ ሆነ ለእናንተ የተቀደሰ ይሁን፤ ሳትዘሩት በሜዳ የበቀለውን ብሉ። “ ‘በዚህ በኢዮቤልዩ ዓመት እያንዳንዱ ሰው ወደ ርስቱ ይመለስ። “ ‘ከወገንህ ከአንዱ መሬት ብትገዛ ወይም ብትሸጥለት፣ አንዱ ሌላውን አያታልል። ከኢዮቤልዩ በኋላ ያሉትን ዓመታት ብዛት መሠረት በማድረግ ከወገንህ ትገዛለህ፤ እርሱም የቀሩትን የመከር ዓመታት ብዛት መሠረት በማድረግ ይሸጥልሃል። የዓመቱ ቍጥር ከበዛ ዋጋውን ጨምር፤ የዓመቱ ቍጥር ካነሰም፣ ዋጋውን ቀንስ፤ ምክንያቱም የሚሸጥልህ የዓመቱን የምርት መጠን ነውና። አንዱ ሌላውን አያታልል፤ አምላክህን ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። “ ‘ሥርዐቴን ጠብቁ፤ ሕጌን በጥንቃቄ አድርጉ፤ በምድሪቱም ያለ ሥጋት ትኖራላችሁ። ምድሪቱ ፍሬዋን ትሰጣለች፤ እስክትጠግቡ ትበላላችሁ፤ በዚያም ያለ ሥጋት ትኖራላችሁ። እናንተም፣ “ካልዘራን ወይም ሰብላችንን ካልሰበሰብን በሰባተኛው ዓመት ምን እንበላለን?” በማለት ትጠይቁ ይሆናል። በስድስተኛው ዓመት በረከቴን እሰድድላችኋለሁ፤ ምድሪቱም ለሦስት ዓመት የሚበቃ ፍሬ ትሰጣለች። በስምንተኛው ዓመት በምትዘሩበት ጊዜ፣ የምትበሉት ቀድሞ ከሰበሰባችሁት ሰብል ይሆናል፤ የዘጠነኛውን ዓመት መከር እስክትሰበስቡ ድረስ ከዚሁ እህል ትበላላችሁ። “ ‘መሬት ለዘለቄታ አይሸጥ፤ ምክንያቱም ምድሪቱ የእኔ ናት፤ እናንተም መጻተኞችና እንግዶች ናችሁ። ርስት አድርጋችሁ በምትይዙት ምድር ሁሉ መሬት የሚዋጅበት ሁኔታ እንዲኖር አድርጉ። “ ‘ከወገንህ አንዱ ደኽይቶ ርስቱን ቢሸጥ፣ የቅርብ ዘመዱ መጥቶ ወገኑ የሸጠውን ይዋጅለት። ነገር ግን ሰውየው ርስቱን የሚዋጅለት ምንም ዘመድ ባይኖረውና እርሱ ራሱ መዋጀት የሚችልበትን ሀብት ቢያገኝ፣ ርስቱን ከሸጠበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን የሽያጭ ዘመን በመቍጠር የዋጋውን ልዩነት ለገዛው ሰው ይመልስ፤ እርሱም ወደ ገዛ ርስቱ ይመለስ። ነገር ግን ዋጋውን መመለስ ካልቻለ፣ የሸጠው ርስት እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ የገዢው ንብረት ሆኖ ይቈያል፤ በኢዮቤልዩ ዓመት ለባለቤቱ ይመለሳል፤ ሰውየውም ወደ ርስቱ ይመለሳል። “ ‘ማንኛውም ሰው ቅጥር በተሠራለት ከተማ ውስጥ የሚገኝ መኖሪያ ቤቱን ቢሸጥ ከሸጠበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አንድ ዓመት ሊዋጀው ይችላል፤ የመዋጀት መብቱ እስከ አንድ ዓመት ድረስ ነው። ሙሉው ዓመት ከማለቁ በፊት መዋጀት ካልቻለ ግን፣ ቅጥር በተሠራለት ከተማ ውስጥ ያለው ቤት የገዢውና የልጅ ልጆቹ ንብረት ሆኖ ይቀራል፤ በኢዮቤልዩ አይመለስለትም። ቅጥር በዙሪያው ባልተሠራለት መንደር ውስጥ የሚገኙ ቤቶች ግን እንደ ዕርሻ መሬት ተቈጥረው ሊዋጁ ይችላሉ፤ በኢዮቤልዩም ይመለሳሉ። “ ‘ነገር ግን ሌዋውያን የራሳቸው በሆኑት ከተሞች ውስጥ የሚገኙትን ቤቶቻቸውን ምን ጊዜም የመዋጀት መብት አላቸው። ሌዋውያን በከተማቸው ያለውን ቤታቸውን ቢሸጡና መዋጀት ባይችሉ፣ በኢዮቤልዩ ይመለሳል፤ በሌዋውያን ከተሞች የሚገኙ ቤቶች በእስራኤላውያን መካከል የሌዋውያን ንብረት ናቸውና። በከተሞቻቸው ዙሪያ ያለው የግጦሽ መሬት ግን አይሸጥ፤ ለዘላለም ቋሚ ንብረታቸው ነውና። “ ‘በመካከልህ ከወገንህ አንዱ ቢደኸይ፣ ራሱንም መርዳት ባይችል፣ በመካከልህ ይኖር ዘንድ መጻተኛውን ወይም እንግዳውን እንደምትረዳ ርዳው። ወገንህ በመካከልህ ይኖር ዘንድ ምንም ዐይነት ወለድ አትቀበለው፤ አምላክህን ፍራው። ገንዘብህን በዐራጣ አታበድረው፤ ምግብህንም በትርፍ አትሽጥለት። የከነዓንን ምድር ልሰጥህና አምላክህ ልሆን፣ ከግብጽ ያወጣሁህ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝ። “ ‘ከወገንህ አንዱ ከመካከልህ ቢደኸይ፣ ራሱንም ለአንተም ቢሸጥ፣ እንደ ባሪያ አድርገህ አታሠራው። በመካከልህ እንዳለ ቅጥር ሠራተኛ ወይም እንደ እንግዳ አድርገህ ቍጠረው፤ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመትም ይሥራልህ፤ ከዚያም በኋላ እርሱና ልጆቹ በነጻ ይለቀቁ፤ ወደ ቤተ ሰቡና ወደ አባቶቹ ንብረት ይመለስ። እስራኤላውያን ከግብጽ ያወጣኋቸው አገልጋዮቼ ስለ ሆኑ እንደ ባሪያ አይሸጡ። በጭካኔ አትግዛቸው፤ ነገር ግን አምላክህን ፍራ። “ ‘የሚኖሩህ ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎችህ፣ በዙሪያህ ካሉት አሕዛብ መካከል የገዛሃቸው ባሪያዎች ይሁኑ። እንደዚሁም በመካከላችሁ ከሚኖሩት መጻተኞችና ከተወለዱት ወገናቸው ባሪያዎችን ግዙ፤ ንብረታችሁም ይሁኑ። እነርሱንም እንደ ንብረት ለልጆቻችሁ አውርሷቸው፤ በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ባሪያዎች ይሁኗችሁ፤ እስራኤላውያን ወገኖቻችሁን ግን በጭካኔ አትግዟቸው። “ ‘በመካከላችሁ የሚኖር መጻተኛ ወይም እንግዳ ሀብታም ቢሆንና ከወገናችሁ አንዱ ደኽይቶ በመካከላችሁ ለሚኖር መጻተኛ ወይም ከመጻተኛው ወገን ለአንዱ ራሱን ቢሸጥ፣ ከተሸጠ በኋላ ሊዋጅ ይችላል። ከዘመዶቹም አንዱ፣ አጎቱ ወይም የአጎቱ ልጅ ወይም ከወገኖቹ ማንኛውም የሥጋ ዘመዱ ይዋጀው፤ ሀብት ካገኘም ራሱን መዋጀት ይችላል። እርሱም ራሱን ከሸጠበት ዓመት አንሥቶ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ያለውን ጊዜ ከገዛው ሰው ጋራ በመሆን ይቍጠር፤ ነጻ የሚለቀቅበትም ዋጋ በእነዚያ ዓመታት ለአንድ ቅጥር ሠራተኛ በሚከፈለው መሠረት ይተመናል። ብዙ ዓመት የሚቀረው ከሆነም፣ እርሱን ለመግዛት ከተከፈለው ዋጋ ላይ በቀረው ዓመት መጠን ለሚዋጅበት መልስ ይክፈል። እስከ ኢዮቤልዩ ድረስ የሚቀረው ጥቂት ዓመት ከሆነም፣ በቀረው ዓመት መጠን የሚዋጅበትን መልስ ይክፈል። ከዓመት እስከ ዓመት እንደ ቅጥር ሠራተኛ ይኑር፤ አሳዳሪውም በፊትህ በጭካኔ አይግዛው። “ ‘ከእነዚህ መንገዶች በአንዱ እንኳ መዋጀት ባይችል፣ እርሱና ልጆቹ በኢዮቤልዩ ዓመት በነጻ ይለቀቁ፤ እስራኤላውያን ለእኔ አገልጋዮቼ ናቸውና። እነርሱ ከግብጽ ምድር ያወጣኋቸው አገልጋዮቼ ናቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
ዘሌዋውያን 25 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘሌዋውያን 25
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘሌዋውያን 25:8-55
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች