ዘሌዋውያን 23:33-43

ዘሌዋውያን 23:33-43 NASV

እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘ሰባተኛውም ወር በገባ በዐሥራ ዐምስተኛው ቀን የእግዚአብሔር የዳስ በዓል ይጀምራል፤ እስከ ሰባት ቀንም ይቈያል። የመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ነውና የተለመደ ተግባራችሁን አታከናውኑበት። ሰባት ቀን መሥዋዕቱን በእሳት ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ በስምንተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ መሥዋዕትን በእሳት ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ የተለመደ ተግባራችሁንም አታከናውኑበት። “ ‘የሚቃጠል መሥዋዕትንና የእህል ቍርባንን፣ መሥዋዕትንና የመጠጥ ቍርባንን በተመደበላቸው ቀን ለእግዚአብሔር በእሳት ለማቅረብ፣ የተቀደሱ ጉባኤዎችን የምታውጁባቸው የእግዚአብሔር በዓላት እነዚህ ናቸው። እነዚህ መሥዋዕቶች ለእግዚአብሔር ሰንበት ከምታቀርቡት፣ ከስጦታችሁ፣ ከስእለታችሁና ከበጎ ፈቃድ ስጦታችሁ በተጨማሪ የምታቀርቧቸው ስጦታዎች ናቸው። “ ‘የምድራችሁን ፍሬ ከሰበሰባችሁ በኋላ በሰባተኛው ወር ከዐሥራ ዐምስተኛው ቀን ጀምራችሁ ሰባት ቀን ለእግዚአብሔር በዓል አክብሩ፤ የመጀመሪያው ቀን የዕረፍት ዕለት ነው፤ ስምንተኛውም ቀን እንደዚሁ የዕረፍት ዕለት ይሆናል። በመጀመሪያው ቀን የመልካም ዛፍ ፍሬ፣ የዘንባባ ዝንጣፊ፣ የለመለመ ዛፍ ቅርንጫፍ የአኻያ ዛፍ ቅርንጫፍ ይዛችሁ ሰባት ቀን በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይበላችሁ። በየዓመቱም የእግዚአብሔር በዓል አድርጋችሁ ሰባት ቀን አክብሩ፤ ይህም ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዐት ነው፤ በሰባተኛውም ወር አክብሩት። ሰባት ቀን ዳስ ውስጥ ተቀመጡ፤ በትውልዱ እስራኤላዊ የሆነ ሁሉ ዳስ ውስጥ ይሰንብት፤ በዚህም እኔ እስራኤላውያንን ከግብጽ ባወጣሁ ጊዜ፣ ዳስ ውስጥ እንዲቀመጡ ማድረጌን የልጅ ልጆቻችሁ ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።’ ”