ዘሌዋውያን 2:1-10

ዘሌዋውያን 2:1-10 NASV

“ ‘ማንኛውም ሰው የእህል ቍርባን ለእግዚአብሔር በሚያቀርብበት ጊዜ፣ ዱቄቱ የላመ ይሁን፤ ዘይት ያፍስስበት፤ ዕጣንም ይጨምርበት፤ ወደ ካህናቱም ወደ አሮን ልጆች ያምጣው። ካህኑ ከላመው ዱቄትና ከዘይቱ አንድ ዕፍኝ ሙሉ ያንሣለት፤ ዕጣኑንም ሁሉ ይውሰደው፤ ይህንም በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ ለመታሰቢያ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው። የተረፈውም የእህሉ ቍርባን ለአሮንና ለልጆቹ ይሰጥ፤ ይህም ለእግዚአብሔር በእሳት ከሚቀርበው ቍርባን እጅግ የተቀደሰ ክፍል ነው። “ ‘በማብሰያ ምድጃ የተጋገረ የእህል ቍርባን በምታቀርብበት ጊዜ፣ ከላመ ዱቄት ተዘጋጅቶ እርሾ ሳይገባበት በዘይት ተለውሶ የተጋገረ ኅብስት ይሁን፤ አለዚያም ያለ እርሾ በሥሡ ተጋግሮ ዘይት የተቀባ ቂጣ ይሁን። የእህል ቍርባንህ በምጣድ የሚጋገር ከሆነ፣ እርሾ ሳይገባበት በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት ቂጣ ይሁን። ቈራርሰህ ዘይት አፍስስበት፤ ይህ የእህል ቍርባን ነው። የእህል ቍርባንህ በመጥበሻ የሚበስል ከሆነ፣ ከላመ ዱቄትና ከዘይት ይዘጋጅ። በዚህ ሁኔታ የተዘጋጀውን የእህል ቍርባን ወደ እግዚአብሔር አምጥተህ ለካህኑ አስረክብ፤ ካህኑም ወደ መሠዊያው ይወስደዋል፤ ካህኑም ከእህሉ ቍርባን ላይ ለመታሰቢያ የሚሆነውን ክፍል ያነሣና በእሳት የሚቃጠል፣ ሽታውም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። የተረፈውም የእህሉ ቍርባን ለአሮንና ለልጆቹ ይሰጥ፤ ይህም ለእግዚአብሔር በእሳት ከሚቀርበው ቍርባን እጅግ የተቀደሰ ክፍል ነው።