ዘሌዋውያን 19:14-32

ዘሌዋውያን 19:14-32 NASV

“ ‘ደንቈሮውን አትርገም፤ በዐይነ ስውሩም ፊት ዕንቅፋት አታኑር፤ ነገር ግን አምላክህን ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። “ ‘ፍርድ አታዛቡ፤ ለድኻው አታድላለት፤ ለትልቁም ሰው ልዩ አክብሮት አትስጥ፤ ለብርቱው አታድላ፤ ነገር ግን ለባልንጀራህ በጽድቅ ፍረድ። “ ‘በሕዝብህ መካከል ሐሜት አትንዛ። “ ‘የባልንጀራህን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውንም ነገር አታድርግ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። “ ‘ወንድምህን በልብህ አትጥላው፤ የበደሉ ተካፋይ እንዳትሆን ባልንጀራህን በግልጽ ገሥጸው። “ ‘ወገንህን አትበቀል፤ ወይም በመካከልህ ከሚኖር በማንኛውም ሰው ላይ ቂም አትያዝ፤ ነገር ግን ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። “ ‘ሥርዐቴን ጠብቁ። “ ‘የተለያዩ እንስሳትን አታዳቅል። “ ‘በዕርሻህ ላይ ሁለት ዐይነት ዘር አትዝራ። “ ‘ከሁለት ዐይነት ነገር የተሠራ ልብስ አትልበስ። “ ‘አንድ ሰው ለሌላ ከታጨች ሴት ባሪያ ጋራ ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ ሴቲቱም ያልተዋጀች ወይም ነጻ ያልወጣች ብትሆን ይቀጣል፤ ነገር ግን ሴቲቱ ነጻ ስላልወጣች አይገደሉም። ሰውየውም ለበደል መሥዋዕት የሚሆን አንድ አውራ በግ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ለእግዚአብሔር ያምጣ። ካህኑም በበደል መሥዋዕቱ አውራ በግ፣ ሰውየው ስለ ሠራው ኀጢአት በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል፤ ኀጢአቱም ይቅር ይባልለታል። “ ‘ወደ ምድሪቱ ገብታችሁ ማንኛውንም ዐይነት ፍሬ የሚሰጥ ዛፍ በምትተክሉበት ጊዜ፣ ፍሬው ለመብላት ያልተገረዘ መሆኑን ዕወቁ፤ ለሦስት ዓመትም የተከለከለ በመሆኑ አይበላ። በአራተኛውም ዓመት ፍሬው ሁሉ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ የምስጋና መሥዋዕት ይሆናል። በዐምስተኛው ዓመት ግን ፍሬውን ትበላላችሁ፤ በዚህም ሁኔታ ፍሬው ይበዛላችኋል፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። “ ‘ደም ያለበትን ማንኛውንም ሥጋ አትብሉ። “ ‘ጥንቈላ ወይም አስማት አትሥሩ። “ ‘የራስ ጠጕራችሁን ዙሪያ አትከርከሙ፤ ጢማችሁንም አሳጥራችሁ አትቍረጡ። “ ‘ለሞተ ሰው ሰውነታችሁን አትንጩ፤ በሰውነታችሁም ላይ ንቅሳት አታድርጉ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። “ ‘ምድሪቱ ወደ ግልሙትና አዘንብላ በርኩሰት እንዳትሞላ፣ ሴት ልጅህ ጋለሞታ ትሆን ዘንድ አታዋርዳት። “ ‘ሰንበታቴን ጠብቁ፤ መቅደሴንም አክብሩ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። “ ‘እንዳትረክሱባቸው ወደ ሙታን ጠሪዎች ዘወር አትበሉ፤ መናፍስት ጠሪዎችንም አትፈልጉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። “ ‘ዕድሜው ለገፋ ተነሥለት፤ ሽማግሌውን አክብር፤ አምላክህንም ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።