ዘሌዋውያን 13:1-8

ዘሌዋውያን 13:1-8 NASV

እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ “ማንኛውም ሰው በሰውነቱ ቈዳ ላይ ዕብጠት ወይም ችፍታ ወይም ቋቍቻ ቢወጣበትና ይህም ወደ ተላላፊ የቈዳ በሽታ የሚለወጥበት ከሆነ፣ ወደ ካህኑ አሮን ወይም ካህናት ከሆኑት ልጆቹ ወደ አንዱ ያምጡት። ካህኑም በሰውየው ቈዳ ላይ ያለውን ቍስል ይመርምር፤ በቍስሉ በተበከለው አካባቢ ያለው ጠጕር ወደ ነጭነት ተለውጦ ቢያገኘውና ቦታው ጐድጕዶ ወደ ውስጥ ቢገባ፣ ይህ ተላላፊ የቈዳ በሽታ ነው። ካህኑም መርምሮ ይህን ባወቀ ጊዜ፣ ሰውየው በአምልኮው ሥርዐት መሠረት ርኩስ መሆኑ ይገለጽ። በቈዳው ላይ ያለው ቋቍቻ ነጭ ሆኖ ቢታይ፣ ነገር ግን ከቈዳው በታች ዘልቆ ባይገባና በቦታው ላይ የሚገኘው ጠጕር ወደ ነጭነት ባይለወጥ፣ ካህኑ በሽተኛውን ሰባት ቀን ያግልለው። በሰባተኛውም ቀን ካህኑ በሽተኛውን ይመርምረው፤ ቍስሉ ለውጥ ካላመጣና በቈዳውም ላይ ካልተስፋፋ እንደ ገና ሰባት ቀን ያግልለው። በሰባተኛው ቀን ካህኑ እንደ ገና ይመርምረው፤ ቍስሉ ከከሰመና በቈዳው ላይ ካልተስፋፋ፣ ካህኑ ሰውየው ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ፤ ቍስሉ ችፍታ እንጂ ሌላ አይደለም። ሰውየው ልብሱን ይጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል። ራሱን ለካህን አሳይቶ መንጻቱ ከታወቀ በኋላ፣ ችፍታው በቈዳው ላይ እየተስፋፋ ከሆነ፣ እንደ ገና ካህኑ ፊት ይቅረብ፤ ካህኑም ይመርምረው፤ ችፍታው በቈዳው ላይ ተስፋፍቶ ከተገኘ፣ ካህኑ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ያስታውቅ፤ ተላላፊ የቈዳ በሽታ ነው።