ዘሌዋውያን 11:39-47

ዘሌዋውያን 11:39-47 NASV

“ ‘እንድትበሉ ከተፈቀደላችሁ እንስሳት አንዱ ቢሞት፣ በድኑን የሚነካ ማንኛውም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። ማንም ሰው ከበድኑ ቢበላ ልብሱን ይጠብ፤ ሆኖም እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው፤ በድኑን የሚያነሣ ልብሱን ይጠብ፤ ሆኖም እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። “ ‘ምድር ለምድር የሚንቀሳቀስ ማንኛውም ፍጡር ጸያፍ ነው፤ አይበላም። ምድር ለምድር የሚንቀሳቀሰውን ፍጡር ሁሉ፣ ይኸውም በደረቱ የሚሳበውን ወይም በአራት እግር የሚሄደውን ወይም ብዙ እግሮች ያሉትን አትብሉ፤ ጸያፍ ነው። በእነዚህ ፍጥረታት ሁሉ ራሳችሁን አስጸያፊ አታድርጉ፤ በእነርሱም ራሳችሁን በማጕደፍ አትርከሱ። እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ተለዩ፤ ቅዱሳንም ሁኑ፤ ምድር ለምድር በሚንቀሳቀስ በማንኛውም ፍጡር ራሳችሁን አታርክሱ። አምላካችሁ እሆን ዘንድ ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ስለዚህ እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ። “ ‘እንስሳትንና አዕዋፍን፣ በውሃ ውስጥ የሚኖሩትንና ምድር ለምድር የሚንቀሳቀሱትን ፍጥረታት ሁሉ በሚመለከት የተሰጠ ሕግ ይህ ነው። በዚህም በርኩሱና በንጹሑ መካከል፣ እንዲሁም ሕይወት ካላቸው ፍጥረታት የሚበሉትንና የማይበሉትን ትለያላችሁ።’ ”