ዘሌዋውያን 11:13-28

ዘሌዋውያን 11:13-28 NASV

“ ‘ከአዕዋፍ ወገን እነዚህን ትጸየፋላችሁ፤ ጸያፍ ስለ ሆኑም አትብሏቸው፦ ንስር፣ የጥንብ አሞራ፣ ግልገል አንሣ፣ ጭላት፣ ማንኛውም ዐይነት ጭልፊት፣ ማንኛውም ዐይነት ቍራ፣ ሰጎን፣ ጠላቋ፣ ዝዪ፣ ማንኛውም ዐይነት በቋል፣ ጕጕት፣ ርኩም፣ ጋጋኖ፣ የውሃ ዶሮ፣ ይብራ፣ ጥንብ አንሣ አሞራ፣ ሽመላ፣ ማንኛውም ዐይነት ሳቢሳ፣ ጃንጁላቴ ወፍና የሌሊት ወፍ። “ ‘ክንፍ ኖሯቸው በአራት እግር የሚንቀሳቀሱ ነፍሳት ሁሉ በእናንተ ዘንድ አስጸያፊዎች ይሁኑ። ነገር ግን ክንፍ ኖሯቸው በአራት እግር ከሚንቀሳቀሱ ነፍሳት መካከል ከምድር በሚፈናጠሩበት እግራቸው አንጓ ያለባቸውን መብላት ትችላላችሁ። ከእነዚህ ማንኛውንም ዐይነት አንበጣ፣ ፌንጣና ኵብኵባ መብላት ትችላላችሁ። ነገር ግን ክንፍ ኖሯቸው በአራት እግር የሚንቀሳቀሱትን ፍጥረታት ተጸየፏቸው። “ ‘ከእነዚህ የተነሣ ትረክሳላችሁ፤ የእነዚህን በድን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። የእነዚህንም በድን የሚያነሣ ሰው ሁሉ ልብሱን ይጠብ፤ ሆኖም እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው። “ ‘ሰኰና ያለው፣ ነገር ግን ሰኰናው ያልተሰነጠቀና የማያመሰኳ ማንኛውም እንስሳ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሁን። የእነዚህንም በድን የሚነካ ሰው ሁሉ ይረክሳል። አራት እግር ካላቸው እንስሳት ሁሉ በመዳፋቸው የሚሄዱት በእናንተ ዘንድ ርኩሳን ናቸው፤ በድናቸውንም የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። የእነዚህን በድን የሚያነሣ ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሆኖም እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ እንስሳቱም በእናንተ ዘንድ ርኩሳን ናቸው።