ወርቁ እንዴት ደበሰ! ንጹሑስ ወርቅ እንዴት ተለወጠ! የከበሩ ድንጋዮች፣ በየመንገዱ ዳር ተበታትነዋል። እንደ ወርቅ ይቈጠሩ የነበሩ፣ የከበሩ የጽዮን ወንዶች ልጆች፣ የሸክላ ሠሪ እጅ እንደ ሠራው፣ እንዴት አሁን እንደ ሸክላ ዕቃ ሆኑ! ቀበሮዎች እንኳን ግልገሎቻቸውን ለማጥባት፣ ጡታቸውን ይሰጣሉ፤ ሕዝቤ ግን በምድረ በዳ እንዳሉ ሰጎኖች፣ ጨካኞች ሆኑ። ከውሃ ጥም የተነሣ፣ የሕፃናት ምላስ ከላንቃቸው ጋራ ተጣበቀ፤ ልጆቹ ምግብ ለመኑ፤ ነገር ግን ማንም አልሰጣቸውም። ምርጥ ምግብ ይበሉ የነበሩ፣ ተቸግረው በየመንገዱ ላይ ተንከራተቱ፤ ሐምራዊ ግምጃ ለብሰው ያደጉ፣ አሁን በዐመድ ክምር ላይ ተኙ። በሕዝቤ ላይ የደረሰው ቅጣት፣ የማንም እጅ ሳይረዳት፣ በድንገት ከተገለበጠችው፣ ሰዶም ላይ ከደረሰው ቅጣት ይልቅ ታላቅ ነው። መሳፍንታቸው ከበረዶ ይልቅ ብሩህ፣ ከወተትም ይልቅ ነጭ ነበሩ፤ ሰውነታቸው ከቀይ ዕንቍ የቀላ፣ መልካቸውም እንደ ሰንፌር ነበር። አሁን ግን ከጥላሸት ይልቅ ጠቍረዋል፤ በመንገድም የሚያውቃቸው የለም፤ ቈዳቸው ከዐጥንታቸው ጋራ ተጣብቋል፤ እንደ ዕንጨትም ደርቀዋል። በራብ ከሚሞቱት ይልቅ፣ በሰይፍ የተገደሉት ይሻላሉ፤ ምግብ በሜዳ ላይ ካለማግኘታቸው የተነሣ፣ በራብ ደርቀው ያልቃሉ። ሕዝቤ ባለቀበት ጊዜ፣ ምግብ እንዲሆኗቸው፣ ርኅሩኆቹ ሴቶች በገዛ እጆቻቸው፣ ልጆቻቸውን ቀቀሉ። እግዚአብሔር ለመቅሠፍቱ መውጫ በር ከፈተ፤ ጽኑ ቍጣውን አፈሰሰ፤ መሠረቷን እንዲበላ፣ በጽዮን እሳት ለኰሰ። ጠላቶችም ሆኑ ወራሪዎች፣ የኢየሩሳሌምን በሮች ጥሰው ይገባሉ ብለው፣ የምድር ነገሥታት፣ ወይም ከዓለም ሕዝብ አንዳቸውም አላመኑም። ይህ ግን ከነቢያት ኀጢአት፣ ከካህናቷም መተላለፍ የተነሣ ሆኗል፤ በውስጧ፣ የጻድቃንን ደም አፍስሰዋልና። እንደ ታወሩ ሰዎች፣ በየመንገዱ ላይ ይደናበራሉ፤ ማንም ሰው ደፍሮ ልብሳቸውን መንካት እስከማይችል ድረስ፣ በደም እጅግ ረክሰዋል። ሰዎች “ሂዱ! እናንተ ርኩሳን!” ብለው ይጮኹባቸዋል፤ “ወግዱ! ወግዱ! አትንኩ!” ይሏቸዋል፤ ሸሽተው በሚቅበዘበዙበትም ጊዜ፣ በአሕዛብ መካከል ያሉ ሰዎች፣ “ከእንግዲህ በዚህ መቀመጥ አይገባቸውም!” ይላሉ። እግዚአብሔር ራሱ በትኗቸዋል፤ ከእንግዲህ ወዲያ አይጠብቃቸውም፤ ካህናቱ አልተከበሩም፤ ሽማግሌዎቹም ከበሬታ አላገኙም። ከሁሉም በላይ በከንቱ ርዳታን ስንጠባበቅ፣ ዐይኖቻችን ደከሙ፤ ከግንብ ማማችን ላይ ሆነን፣ ሊያድን ከማይችል ሕዝብ ርዳታ ጠበቅን። ሰዎች እግር እግራችንን ተከታተሉን፤ ስለዚህ በመንገዳችን መሄድ አልቻልንም፤ መጨረሻችን ቀርቧል፤ ቀኖቻችንም ተቈጥረዋል፤ ፍጻሜያችን መጥቷልና። ከሰማይ ንስሮች ይልቅ፣ ጠላቶቻችን ፈጣኖች ናቸው፤ በተራሮች ላይ አሳደዱን፤ በምድረ በዳም ሸመቁብን። በእግዚአብሔር የተቀባው፣ የሕይወታችን እስትንፋስ፣ በወጥመዳቸው ተያዘ፤ በጥላው ሥር፣ በአሕዛብ መካከል እንኖራለን ብለን አስበን ነበር። አንቺ በዖፅ ምድር የምትኖሪ፣ የኤዶምያስ ሴት ልጅ ሆይ፤ ደስ ይበልሽ፤ ሐሤትም አድርጊ፤ ነገር ግን ለአንቺም ደግሞ ጽዋው ይደርስሻል፤ ትሰክሪያለሽ፤ ዕርቃንሽንም ትጋለጫለሽ። የጽዮን ልጅ ሆይ፤ ቅጣትሽ ያበቃል፤ እርሱም የስደትሽን ዘመን አያራዝምም፤ ነገር ግን አንቺ የኤዶምያስ ልጅ ሆይ፤ ኀጢአትሽን ይቀጣል፤ ክፋትሽንም ይፋ ያወጣል።
ሰቈቃወ 4 ያንብቡ
ያዳምጡ ሰቈቃወ 4
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሰቈቃወ 4:1-22
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች