ሰቈቃወ 3:21-66

ሰቈቃወ 3:21-66 NASV

ሆኖም ይህን ዐስባለሁ፤ እንግዲያስ ተስፋ አለኝ፤ ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ታላቅ ፍቅር የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና። ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤ ታማኝነትህም ብዙ ነው። ራሴን እንዲህ አልሁት፤ “እግዚአብሔር ዕድል ፈንታዬ ነው፤ ስለዚህ ተስፋ አደርገዋለሁ።” እርሱን ተስፋ ለሚያደርጉት፣ ለሚፈልገውም ሰው እግዚአብሔር መልካም ነው። ሰው የእግዚአብሔርን ማዳን፣ ዝም ብሎ ተስፋ ቢያደርግ መልካም ነው። ሰው በወጣትነቱ፣ ቀንበር ቢሸከም መልካም ነው። ብቻውን ዝም ብሎ ይቀመጥ፤ እግዚአብሔር አሸክሞታልና። ፊቱን በዐቧራ ውስጥ ይቅበር፤ ተስፋ ሊኖር ይችላልና። ጕንጩን ለሚመታው ሰው ይስጥ፤ ውርደትንም ይጥገብ። ጌታ ሰውን፣ ለዘላለም አይጥልምና፤ መከራን ቢያመጣ እንኳ ይራራል፤ ታላቅ ፍቅሩ አይለወጥምና። ሆነ ብሎ ችግርን፣ ወይም መከራን በሰው ልጆች ላይ አያመጣምና። የምድሪቱ እስረኞች ሁሉ፣ በእግር ሲረገጡ፣ በልዑል ፊት፣ ሰው መብቱ ሲነፈገው፣ ሰው ፍትሕ ሲጓደልበት፣ ጌታ እንዲህ ዐይነቱን ነገር አያይምን? ጌታ ካላዘዘ በቀር፣ ተናግሮ መፈጸም የሚችል ማን ነው? ክፉም ሆነ መልካም ነገር፣ ከልዑል አፍ የሚወጣ አይደለምን? ታዲያ ሕያው ሰው በኀጢአቱ ሲቀጣ፣ ስለ ምን ያጕረመርማል? መንገዳችንን እንመርምር፤ እንፈትን፤ ወደ እግዚአብሔርም እንመለስ። ልባችንን ከእጃችን ጋራ በሰማይ ወዳለው ወደ አምላካችን እናንሣ፤ እንዲህም እንበል፤ “ዐምፀናል፤ ኀጢአትም ሠርተናል፤ አንተም ይቅር አላልኸንም። “ራስህን በቍጣ ከደንህ፤ አሳደድኸንም፤ ያለ ርኅራኄም ገደልኸን። ጸሎት እንዳያልፍ፣ ራስህን በደመና ሸፈንህ። በአሕዛብ መካከል፣ አተላና ጥራጊ አደረግኸን። “ጠላቶቻችን ሁሉ፣ አፋቸውን በእኛ ላይ ከፈቱ። በጥፋትና በመፈራረስ፣ በችግርና በሽብር ተሠቃየን።” የእንባ ጐርፍ ከዐይኔ ፈሰሰ፤ ሕዝቤ ዐልቋልና። ያለ ዕረፍት፣ ያለ ማቋረጥ ዐይኖቼ እንባ ያፈስሳሉ፤ እግዚአብሔር ከላይ፣ ከሰማይ እስኪያይ ድረስ። በከተማዬ ባሉት ሴቶች ሁሉ ላይ የደረሰውን ማየቴ፣ ነፍሴን አስጨነቃት። ያለ ምክንያት ጠላቶቼ የሆኑ፣ እንደ ወፍ ዐደኑኝ። ሕይወቴን በጕድጓድ ውስጥ ሊያጠፉ ሞከሩ፣ ድንጋይም በላዬ አደረጉ። ውሃ ሞልቶ በዐናቴ ላይ ፈሰሰ፤ ጠፍቻለሁ ብዬ አሰብሁ። በጥልቁ ጕድጓድ ውስጥ ሳለሁ፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ የአንተን ስም ጠራሁ። ልመናዬን ሰምተሃል፤ “ርዳታም ፈልጌ ስጮኽ፣ ከመስማት ጆሮህን አትከልክል።” በጠራሁህ ጊዜ ቀረብኸኝ፣ እንዲሁም፣ “አትፍራ” አልኸኝ። ጌታ ሆይ፤ ለእኔ ተሟገትኽልኝ፤ ሕይወቴንም ተቤዠህ። እግዚአብሔር ሆይ፤ በእኔ ላይ የተደረገውን ግፍ አየህ፤ ፍርዴን ፍረድልኝ! በቀላቸውን ሁሉ፣ በእኔም ላይ ያሰቡትን ዐድማ አየህ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ስድባቸውን ሁሉ፣ በእኔ ላይ ያሰቡትን ዐድማ ሁሉ ሰማህ፤ ይህም ቀኑን ሙሉ በእኔ ላይ፣ ጠላቶቼ የሚያውጠነጥኑትና የሚያንሾካሹኩት ነው። ተመልከታቸው! ቆመውም ሆነ ተቀምጠው፣ በዘፈናቸው ይሣለቁብኛል። እግዚአብሔር ሆይ፤ እጆቻቸው ላደረጉት፣ የሚገባውን መልሰህ ክፈላቸው። በልባቸው ላይ መጋረጃን ዘርጋ፤ ርግማንህም በላያቸው ይሁን! ከእግዚአብሔር ሰማያት በታች፣ በቍጣህ አሳድዳቸው፤ አጥፋቸውም።