ሰቈቃወ 1:1-7

ሰቈቃወ 1:1-7 NASV

በሕዝብ ተሞልታ የነበረችው ከተማ፣ እንዴት የተተወች ሆና ቀረች! በሕዝቦች መካከል ታላቅ የነበረችው፣ እርሷ እንዴት እንደ መበለት ሆነች! በአውራጃዎች መካከል ልዕልት የነበረችው፣ አሁን ባሪያ ሆናለች። በሌሊት አምርራ ታለቅሳለች፤ እንባዋ በጕንጮቿ ላይ ይወርዳል፤ ከወዳጆቿ ሁሉ መካከል፣ የሚያጽናናት ማንም የለም፤ ባልንጀሮቿ ሁሉ ከድተዋታል፤ ጠላቶቿም ሆነዋል። በመከራና በመረገጥ ብዛት ይሁዳ ተማርካ ሄደች፤ በሕዝቦችም መካከል ተቀመጠች፤ የምታርፍበትንም ስፍራ ዐጣች፤ በጭንቀቷ መካከል ሳለች፣ አሳዳጆቿ ሁሉ አገኟት። የጽዮን መንገዶች ያለቅሳሉ፤ በዓላቷን ለማክበር የሚመጣ የለምና፤ በበሮቿ ሁሉ የሚገባና የሚወጣ የለም፤ ካህናቷ ይቃትታሉ፤ ደናግሏ ክፉኛ ዐዝነዋል፤ እርሷም በምሬት ትሠቃያለች። ባላጋሮቿ ገዦቿ ሆኑ፤ ጠላቶቿ ተመችቷቸዋል፤ ከኀጢአቷ ብዛት የተነሣ፣ እግዚአብሔር ከባድ ሐዘን አምጥቶባታል። ልጆቿ በጠላት ፊት ተማርከው፣ ወደ ግዞት ሄደዋል። የጽዮን ሴት ልጅ፣ ግርማ ሞገሷ ሁሉ ተለይቷታል፤ መሳፍንቷ፣ መሰማሪያ እንዳጣ ዋሊያ ናቸው፤ በአሳዳጆቻቸው ፊት፣ በድካም ሸሹ። በተጨነቀችባቸውና በተንከራተተችባቸው ቀናት፣ ኢየሩሳሌም በጥንት ዘመን የነበራትን፣ ሀብት ሁሉ ታስባለች፤ ሕዝቦቿ በጠላት እጅ በወደቁ ጊዜ፣ የረዳት ማንም አልነበረም፤ ጠላቶቿ ተመለከቷት፤ በመፈራረሷም ሣቁ።