በሕዝብ ተሞልታ የነበረችው ከተማ፣ እንዴት የተተወች ሆና ቀረች! በሕዝቦች መካከል ታላቅ የነበረችው፣ እርሷ እንዴት እንደ መበለት ሆነች! በአውራጃዎች መካከል ልዕልት የነበረችው፣ አሁን ባሪያ ሆናለች። በሌሊት አምርራ ታለቅሳለች፤ እንባዋ በጕንጮቿ ላይ ይወርዳል፤ ከወዳጆቿ ሁሉ መካከል፣ የሚያጽናናት ማንም የለም፤ ባልንጀሮቿ ሁሉ ከድተዋታል፤ ጠላቶቿም ሆነዋል። በመከራና በመረገጥ ብዛት ይሁዳ ተማርካ ሄደች፤ በሕዝቦችም መካከል ተቀመጠች፤ የምታርፍበትንም ስፍራ ዐጣች፤ በጭንቀቷ መካከል ሳለች፣ አሳዳጆቿ ሁሉ አገኟት። የጽዮን መንገዶች ያለቅሳሉ፤ በዓላቷን ለማክበር የሚመጣ የለምና፤ በበሮቿ ሁሉ የሚገባና የሚወጣ የለም፤ ካህናቷ ይቃትታሉ፤ ደናግሏ ክፉኛ ዐዝነዋል፤ እርሷም በምሬት ትሠቃያለች። ባላጋሮቿ ገዦቿ ሆኑ፤ ጠላቶቿ ተመችቷቸዋል፤ ከኀጢአቷ ብዛት የተነሣ፣ እግዚአብሔር ከባድ ሐዘን አምጥቶባታል። ልጆቿ በጠላት ፊት ተማርከው፣ ወደ ግዞት ሄደዋል። የጽዮን ሴት ልጅ፣ ግርማ ሞገሷ ሁሉ ተለይቷታል፤ መሳፍንቷ፣ መሰማሪያ እንዳጣ ዋሊያ ናቸው፤ በአሳዳጆቻቸው ፊት፣ በድካም ሸሹ። በተጨነቀችባቸውና በተንከራተተችባቸው ቀናት፣ ኢየሩሳሌም በጥንት ዘመን የነበራትን፣ ሀብት ሁሉ ታስባለች፤ ሕዝቦቿ በጠላት እጅ በወደቁ ጊዜ፣ የረዳት ማንም አልነበረም፤ ጠላቶቿ ተመለከቷት፤ በመፈራረሷም ሣቁ። ኢየሩሳሌም ከባድ ኀጢአት ሠርታለች፤ ስለዚህም የረከሰች ሆናለች፤ ያከበሯት ሁሉ ናቋት፤ ዕራቍቷን ሆና አይተዋታልና፤ እርሷ ራሷ ታጕረመርማለች፤ ወደ ኋላዋም ዘወር ብላለች። ርኩሰቷ በቀሚሷ ላይ ታየ፤ ወደ ፊት የሚሆንባትን አላሰበችም፤ አወዳደቋ አስደንጋጭ ሆነ፤ የሚያጽናናትም አልነበረም፤ “እግዚአብሔር ሆይ፤ መከራዬን ተመልከት፤ ጠላት ድል አድርጓልና!” ዮድ በሀብቷ ሁሉ ላይ፣ ጠላት እጁን ዘረጋ፤ ወደ ጉባኤህ እንዳይገቡ የከለከልሃቸው፣ ጣዖት የሚያመልኩ አሕዛብ፣ ወደ መቅደሷ ሲገቡ አየች። እንጀራ በመፈለግ፣ ሕዝቧ ሁሉ በሥቃይ ይጮኻል፤ በሕይወት ለመኖር፣ የከበረ ሀብታቸውን በምግብ ይለውጣሉ፤ “አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ አስበኝ፤ ተመልከተኝም፤ እኔ ተዋርጃለሁና።” “እናንተ መንገድ ዐላፊዎች ሁሉ፤ ይህ ለእናንተ ምንም አይደለምን? ተመልከቱ፤ እዩም፤ በጽኑ ቍጣው ቀን፣ እግዚአብሔር ያመጣብኝን፣ በእኔ ላይ የደረሰውን፣ የእኔን መከራ የመሰለ መከራ አለን? “ከከፍታ ስፍራ እሳትን ላከ፤ ወደ ታች ወደ ዐጥንቶቼም ሰደደው፤ በእግሮቼ ላይ መረብ ዘረጋ፤ ወደ ኋላም ጣለኝ፤ ቀኑን ሙሉ በማድከም፣ ባዶ አድርጎ አስቀመጠኝ። “ኀጢአቶቼ ቀንበር ሆኑ፤ በእጆቹ አንድ ላይ ተገመዱ፤ በዐንገቴም ላይ ተጭነዋል፤ ኀይሌንም አዳከመ፤ ልቋቋማቸው ለማልችላቸው፣ እርሱ አሳልፎ ሰጠኝ። “በውስጤ ያሉትን ጦረኞችህ ሁሉ፣ እግዚአብሔር ተቃወመ፤ ጕልማሶቼን ለማድቀቅ፣ ሰራዊት በላዬ ላይ ጠራ፤ ድንግሊቱን የይሁዳ ሴት ልጅ፣ እግዚአብሔር በወይን መጭመቂያ ውስጥ ረገጣት። “የማለቅሰው ስለ እነዚህ ነገሮች ነው፤ ዐይኖቼ በእንባ ተሞልተዋል፣ ሊያጽናናኝ የቀረበ፣ መንፈሴንም ሊያረጋጋ የሞከረ ማንም የለም፤ ጠላት በርትቷልና ልጆቼ ተጨንቀዋል።” ጽዮን እጆቿን ዘረጋች፤ የሚያጽናናትም የለም፤ ጎረቤቶቹ ጠላቶቹ እንዲሆኑ፣ እግዚአብሔር በያዕቆብ ላይ ትእዛዝ አውጥቷል፤ ኢየሩሳሌምም በመካከላቸው፣ እንደ ርኩስ ነገር ተቈጠረች። “እግዚአብሔር ጻድቅ ነው፤ እኔ ግን በትእዛዙ ላይ ዐመፅ አድርጌ ነበር፤ እናንተ ሕዝቦች ሁሉ ስሙ፤ መከራዬንም ተመልከቱ፤ ወይዛዝርቶቼና ጐበዛዝቴ፣ ተማርከው ሄደዋል።
ሰቈቃወ 1 ያንብቡ
ያዳምጡ ሰቈቃወ 1
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሰቈቃወ 1:1-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች