ኢያሱ 9:1-15

ኢያሱ 9:1-15 NASV

በዮርዳኖስ ምዕራብ ባለው በተራራማው አገር፣ በቈላማው ምድር እንዲሁም እስከ ሊባኖስ በሚደርሰው በመላው በታላቁ ባሕር ዳርቻ የነበሩት የኬጢያውያን፣ የአሞራውያን፣ የከነዓናውያን፣ የፌርዛውያን፣ የኤዊያውያን፣ የኢያቡሳውያን ነገሥታት ይህን በሰሙ ጊዜ፣ ኢያሱንና እስራኤልን ለመውጋት በአንድነት መጡ። የገባዖን ሰዎች ግን ኢያሱ በኢያሪኮና በጋይ ላይ ያደረገውን በሰሙ ጊዜ፣ ለማታለል ፈለጉ፤ ስለዚህም ያረጀ ስልቻና የተጣፈ አሮጌ የወይን ጠጅ አቍማዳ በአህያ የጫነ መልእክተኛ መስለው ሄዱ። ሰዎቹም ያረጀና የተጠጋገነ ነጠላ ጫማ አድርገዋል፤ አሮጌ ልብስ ለብሰዋል፤ ለስንቅ የያዙት እንጀራም በሙሉ የደረቀና የሻገተ ነበር። ከዚያም ኢያሱ ወደ ሰፈረበት ወደ ጌልገላ ሄደው ኢያሱንና የእስራኤልን ሰዎች፣ “የመጣነው ከሩቅ አገር ነው፤ ከእኛ ጋራ ቃል ኪዳን ግቡ” አሏቸው። የእስራኤልም ሰዎች ለኤዊያውያኑ፣ “እናንተ የምትኖሩት እዚሁ ቅርብ ቢሆንስ? ታዲያ ከእናንተ ጋራ እንዴት ቃል ኪዳን እንገባለን?” አሏቸው። እነርሱም ኢያሱን፣ “እኛ ባሪያዎችህ ነን” አሉት። ኢያሱ ግን፣ “እናንተ እነማን ናችሁ? የመጣችሁትስ ከየት ነው?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም እንዲህ ብለው መለሱለት፤ “እኛ ባሪያዎችህ የአምላካህን የእግዚአብሔርን ዝና ሰምተን፣ እጅግ ሩቅ ከሆነ አገር መጥተናል፤ ዝናውንና በግብጽ ያደረገውንም ሁሉ ሰምተናል፤ እንዲሁም ከዮርዳኖስ ማዶ ባሉት በሁለቱ የአሞራውያን ነገሥታት ማለትም በሐሴቦን ንጉሥ በሴዎን፣ አስታሮትን ይገዛ በነበረው በባሳን ንጉሥ በዐግ ያደረገውን ሁሉ ነው። ሽማግሌዎቻችንና በአገራችን የሚኖሩት ሁሉ፣ ‘ለመንገዳችሁ የሚሆን ስንቅ ያዙ፤ ሄዳችሁም ተገናኟቸው፤ “እኛ ባሮቻችሁ እንሆናለን፤ ከእኛ ጋራ ቃል ኪዳን ግቡ” በሏቸው’ አሉን። ይህ የያዝነው እንጀራ ወደ እናንተ ለመምጣት ከቤታችን በተነሣንበት ቀን ትኵስ ነበር፤ አሁን ግን እንዴት እንደ ደረቀና እንደ ሻገተ ተመልከቱ። እነዚህ የወይን ጠጅ አቍማዳዎቻችን ያን ጊዜ ስንሞላቸው አዲስ ነበሩ፤ አሁን ግን እንዴት እንደ ተቀዳደዱ ተመልከቱ፤ ልብሳችንና ጫማችንም ብዙ መንገድ በመጓዛችን ዐልቀዋል።” የእስራኤልም ሰዎች ከስንቃቸው ላይ ጥቂት ወሰዱ፤ ስለ ጕዳዩ ግን እግዚአብሔርን አልጠየቁም ነበር። ኢያሱም በሰላም ለመኖር የሚያስችላቸውን ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋራ አደረገ፤ የጉባኤውም መሪዎች ይህንኑ በመሐላ አጸኑላቸው።