እግዚአብሔርም ኢያሱን፣ “ከተማዪቱን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፣ የያዝኸውን ጦር ወደ ጋይ አነጣጥር” አለው፤ ኢያሱም ጦሩን ወደ ጋይ አነጣጠረ። ይህን እንዳደረገም ያደፈጡት ሰዎች ከተደበቁበት ስፍራ በፍጥነት ወጥተው ወደ ፊት ሮጡ፤ ገብተው ከተማዪቱን ያዟት፤ ወዲያውኑም በእሳት አቃጠሏት። የጋይ ሰዎች ወደ ኋላ ዞረው ሲመለከቱ የከተማዪቱ ጢስ ወደ ሰማይ ሲወጣ አዩ፤ ወደ ምድረ በዳ ይሸሹ የነበሩት እስራኤላውያን ፊታቸውን ስላዞሩባቸውም፣ በየትኛውም በኩል ማምለጫ መንገድ አልነበራቸውም። ኢያሱና እስራኤል ሁሉ ያደፈጠው ጦር ከተማዪቱን መያዙንና ጢሱ ወደ ላይ መውጣቱን ሲያዩ፣ ወደ ኋላ ተመልሰው በጋይ ሰዎች ላይ አደጋ ጣሉባቸው፤ ያደፈጡትም ሰዎች እንደዚሁ ከከተማዪቱ ወጥተው መጡባቸው። ስለዚህ እስራኤላውያን በዚያም በዚህም ስለ ከበቧቸው የጋይን ሰዎች ከመካከል አደረጓቸው፤ እስራኤላውያንም ሰዎቹን ፈጇቸው፤ አንድ እንኳ የተረፈ ወይም ያመለጠ አልነበረም፤ ነገር ግን የጋይን ንጉሥ ከነሕይወቱ ይዘው ወደ ኢያሱ አመጡት። እስራኤላውያን የጋይን ወንዶች ሁሉ ባሳደዷቸው ሜዳና ምድረ በዳ ከጨረሷቸውና እያንዳንዳቸውንም በሰይፍ ከፈጁ በኋላ፣ ወደ ከተማዪቱ ተመልሰው በዚያ ያገኙትን ሁሉ ገደሉ። በዚያች ዕለት የጋይ ሰዎች ሁሉ ዐለቁ፤ የወንዶቹና የሴቶቹም ብዛት ዐሥራ ሁለት ሺሕ ነበር። ኢያሱ በጋይ የሚኖሩትን ሰዎች ሁሉ ፈጽሞ እስኪያጠፋቸው ድረስ ጦር ያነጣጠረባትን እጁን አላጠፈም ነበር። እስራኤላውያንም እግዚአብሔር ኢያሱን ባዘዘው መሠረት፣ በከተማዪቱ ያገኙትን እንስሳትና ምርኮ ብቻ ለራሳቸው አደረጉ። ስለዚህ ኢያሱ ጋይን አቃጠላት፤ እስከ ዛሬ እንደሚታየውም ለዘላለም የዐመድ ቍልልና ባድማ አደረጋት። የጋይንም ንጉሥ በዛፍ ላይ ሰቀለው፤ ሬሳውንም እስኪመሽ ድረስ እዚያው እንዳለ ተወው፤ ፀሓይ ስትጠልቅም፣ ኢያሱ ሬሳውን እንዲያወርዱትና በከተማው በር ላይ እንዲጥሉት አዘዘ፤ የትልልቅ ድንጋይ ቍልልም ከመሩበት፤ ይህም እስከ ዛሬ ድረስ እዚያው ይገኛል።
ኢያሱ 8 ያንብቡ
ያዳምጡ ኢያሱ 8
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኢያሱ 8:18-29
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች