ኢያሱ 17:14-18

ኢያሱ 17:14-18 NASV

የዮሴፍ ዘሮች ኢያሱን፣ “ቍጥራችን ብዙ ነው፤ እግዚአብሔርም አብዝቶ ባርኮናል፤ ታዲያ እንዴት ርስታችን አንድ ዕጣና አንድ ድርሻ ብቻ ሆነ?” አሉት። ኢያሱም መልሶ፣ “ቍጥራችሁ ይህን ያህል በዝቶ ኰረብታማው የኤፍሬም ምድር እስከዚህ የሚጠብባችሁ ከሆነ፣ ወደ ፌርዛውያንና ወደ ራፋይም ምድር ወጥታችሁ ደኑን ለራሳችሁ መንጥሩ” አላቸው። የዮሴፍም ዘሮች፣ “ኰረብታማው አገር አይበቃንም፤ ደግሞም በሜዳው ላይ ያሉት በቤትሳንና በሰፈሮቿ፣ እንዲሁም በኢይዝራኤል ሸለቆ የሚኖሩት ከነዓናውያን ሁሉ የብረት ሠረገሎች አሏቸው” አሉት። ኢያሱ ግን ለዮሴፍ ዘሮች ለኤፍሬምና ለምናሴ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ ቍጥራችሁ ብዙ፣ እጅግም ኀያል እንደ መሆናችሁ ድርሻችሁ አንድ ብቻ አይሆንም፤ ነገር ግን ደን የለበሰው ኰረብታማው አገር የእናንተ ነው፤ ሄዳችሁ መንጥሩት፣ ዳር ድንበሩ ሁሉ የእናንተ ይሆናል፤ ከነዓናውያን የብረት ሠረገላ ቢኖራቸውና ብርቱዎች ቢሆኑም እንኳ ከዚያ ታስወጧቸዋላችሁ።”