ኢያሱ 13:15-33

ኢያሱ 13:15-33 NASV

ሙሴ በየጐሣቸው መድቦ ለሮቤል ነገድ የሰጠው ርስት ይህ ነው፤ ድንበራቸው ከአርኖን ሸለቆ ዳርቻ ካለው ከአሮዔርና ከሸለቆው መካከል ካለችው ከተማ አንሥቶ ያለው ግዛት ሲሆን፣ ሜድባ አጠገብ ያለውን ደጋውን አገር በሙሉ፣ ሐሴቦንና በደጋው ላይ ያሉትን ከተሞቿን በሙሉ፣ እንዲሁም ዲቦንን፣ ባሞትባኣልን፣ ቤትበኣልምዖን፣ ያሀጽን፣ ቅዴሞትን፣ ሜፍዓትን፣ ቂርያታይምን፣ ሴባማን፣ በሸለቆው ኰረብታ ላይ ያለችውን ጼሬትሻሐርን፣ ቤተ ፌጎርን፣ የፈስጋን ሸንተረሮችና ቤትየሺሞትን፣ ማለት በደጋው አገር የሚገኙት ከተሞች ሁሉና መቀመጫውን በሐሴቦን አድርጎ የገዛውን የአሞራውያንን ንጉሥ የሴዎንን ግዛት በሙሉ ያካትታል። ሙሴ ሴዎንንና በዚያው ምድር ተቀማጭ የነበሩትን መሳፍንት፤ ኤዊ፣ ሮቆም፣ ሱር፣ ሑርና ሪባ የተባሉትን የምድያም አለቆች ድል አደረጋቸው። በጦር ሜዳ ከሞቱት ሌላ እስራኤላውያን የቢዖርን ልጅ ሟርተኛውን በለዓምን በሰይፍ መትተው ገደሉት። የሮቤል ነገድ ወሰን የዮርዳኖስ ወንዝ ነው። የሮቤል ነገድ በየጐሣቸው የወረሷቸው ከተሞችና መንደሮቻቸው እነዚህ ነበሩ፤ ሙሴ በየጐሣቸው መድቦ ለጋድ ነገድ የሰጠው ርስት ይህ ነው፤ ድንበራቸው ኢያዜር፣ የገለዓድን ከተሞች በሙሉ በረባት አጠገብ እስካለው እስከ አሮዔር የሚደርሰውን የአሞናውያን አገር እኩሌታ፣ ከሐሴቦን እስከ ራማት ምጽጳና ከዚያም እስከ ብጦኒም፣ ከመሃናይም እስከ ደቤር ግዛት ያለውን፣ በሸለቆው ውስጥ ደግሞ ቤትሀራምን፣ ቤትኒምራን፣ ሱኮትን፣ ዳፎንንና እስከ ኪኔሬት ባሕር ጫፍ የሚደርሰውን ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ ያለውን ቀሪውን የሐሴቦን ንጉሥ የሴዎንን ግዛት ያካትታል። የጋድ ነገድ በየጐሣቸው የወረሷቸው ከተሞችና መንደሮቻቸው እነዚህ ነበሩ። ሙሴ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ማለት ለገሚሱ የምናሴ ቤተ ሰብ ዘሮች በየጐሣቸው የሰጣቸው ርስት ይህ ነው፤ ድንበራቸው ከመሃናይም አንሥቶ ባሳንን በሙሉ ይጨምርና፣ በባሳን ያሉትን ስድሳ የኢያዕር ከተሞች ሁሉ ይዞ የባሳን ንጉሥ የዐግን ግዛት ሁሉ የሚያካትት ሲሆን፣ የገለዓድን እኩሌታ፣ በባሳን የዐግ መንግሥት ዋና ከተማ የሆኑትን አስታሮትንና ኤድራይን ይጨምራል። እነዚህ ለምናሴ ልጅ ለማኪር ዘሮች የተሰጡ ሲሆን፣ ይህም ለግማሾቹ የማኪር ልጆች በየጐሣቸው የተሰጡ ናቸው። ሙሴ ከኢያሪኮ በስተምሥራቅ፣ ከዮርዳኖስ ማዶ በሞዓብ ሜዳ ሳለ የሰጣቸው ርስት ይህ ነበር። ለሌዊ ነገድ ግን ሙሴ ርስት አልሰጠም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንደ ተናገራቸው እርሱ ራሱ ርስታቸው ነውና።