ኢያሱ 1:10-18

ኢያሱ 1:10-18 NASV

ኢያሱም የሕዝቡን አለቆች እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “ወደ ሰፈር ግቡ፤ ለሕዝቡም፣ ‘ስንቃችሁን አዘጋጁ፤ ከአሁን ጀምሮ ባሉት ሦስት ቀናት ውስጥ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ፣ እግዚአብሔር አምላካችሁ ርስት አድርጎ የሚሰጣችሁን ምድር ገብታችሁ ትወርሳላችሁ’ በሏቸው።” ኢያሱ የሮቤልን ነገድ፣ የጋድን ነገድና የምናሴን ነገድ እኩሌታ እንዲህ አላቸው፤ “የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ እንዲህ ሲል የሰጣችሁን ትእዛዝ አስቡ፤ ‘እግዚአብሔር አምላካችሁ ያሳርፋችኋል፤ ይህችንም ምድር ይሰጣችኋል።’ ሚስቶቻችሁና ልጆቻችሁ እንዲሁም ከብቶቻችሁ ሙሴ በሰጣችሁ ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ ባለው ምድር ይቈዩ፤ ነገር ግን ተዋጊዎቻችሁ ሁሉ፣ ከነሙሉ ትጥቃቸው፣ ከወንድሞቻችሁ ቀድመው ይሻገሩ፤ እናንተም ከወንድሞቻችሁ ጐን ተሰለፉ። ይህም፣ እግዚአብሔር እስኪያሳርፋቸውና ለእናንተም እንዳደረገው ሁሉ፣ እነርሱም እግዚአብሔር አምላካችሁ የሰጣቸውን ምድር እስኪወርሱ ድረስ ነው። ከዚህ በኋላ እናንተም ተመልሳችሁ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ የሰጣችሁን፣ በፀሓይ መውጫ ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ ያለውን ምድር ትወርሳላችሁ።” እነርሱም ለኢያሱ እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “ያዘዝኸንን ሁሉ እናደርጋለን፤ ወደምትልከንም ሁሉ እንሄዳለን። ለሙሴ ሙሉ በሙሉ እንደ ታዘዝን ሁሉ፣ ለአንተም እንታዘዛለን፤ ብቻ እግዚአብሔር አምላክህ ከሙሴ ጋራ እንደ ነበረ፣ አሁንም ከአንተ ጋራ ይሁን። በትእዛዝህ ላይ የሚያምፅና ለቃልህ የማይታዘዝ ሁሉ ይገደል፤ ብቻ አንተ ጽና፤ አይዞህ፤ በርታ።”

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}