እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል ይመልስላቸዋል፤ “እህል፣ አዲስ የወይን ጠጅና ዘይት፣ እስክትጠግቡ ድረስ እሰጣችኋለሁ፤ የሕዝቦች መዘባበቻ አላደርጋችሁም። “የሰሜንን ሰራዊት ከእናንተ አርቃለሁ፤ ፊቱን ወደ ምሥራቁ ባሕር፣ ጀርባውንም ወደ ምዕራቡ ባሕር በማድረግ፣ ወደ ደረቀውና ወደ ባድማው ምድር እገፋዋለሁ፤ ግማቱ ይወጣል፤ ክርፋቱም ይነሣል።” በርግጥ እርሱ ታላቅ ነገር አድርጓል። ምድር ሆይ፤ አትፍሪ፤ ደስ ይበልሽ፤ ሐሤትም አድርጊ፤ በርግጥ እግዚአብሔር ታላቅ ነገር አድርጓል። የዱር እንስሳት ሆይ፤ አትፍሩ፤ መሰማሪያ መስኮቹ ለምልመዋልና፤ ዛፎቹ ፍሬአቸውን አፍርተዋል፤ የበለሱ ዛፍና የወይኑ ተክልም እጅግ አፍርተዋል። የጽዮን ሰዎች ሆይ፤ ደስ ይበላችሁ፤ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ሐሤት አድርጉ፤ የበልግን ዝናብ፣ በጽድቅ ሰጥቷችኋልና፤ እንደ ቀድሞውም፣ የበልግንና የጸደይን ዝናብ በብዛት ልኮላችኋል። ዐውድማዎቹ በእህል ይሞላሉ፤ መጥመቂያ ጕድጓዶችም በአዲስ የወይን ጠጅና በዘይት ተሞልተው ያፈስሳሉ። “በመካከላችሁ የሰደድሁት ታላቁ ሰራዊት፣ ትልልቁ አንበጣና ትንንሹ አንበጣ፣ ሌሎች አንበጦችና የአንበጣው መንጋ የበላውን፣ እነዚህ ሁሉ የበሏቸውን ዓመታት ዋጋ እመልስላችኋለሁ። እስክትጠግቡ የምትበሉት ብዙ ምግብ ይኖራችኋል፤ ድንቅ ነገሮችን ለእናንተ የሠራውን፣ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ስም ታመሰግናላችሁ፤ ሕዝቤም ከእንግዲህ ወዲያ አያፍርም። ከዚያም እኔ በእስራኤል መካከል እንዳለሁ፣ እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ፣ እንደ እኔም ያለ፣ ሌላ እንደሌለ ታውቃላችሁ፤ ሕዝቤም ከእንግዲህ ወዲያ አያፍርም። “ከዚህም በኋላ፣ መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፤ ጕልማሶቻችሁም ራእይ ያያሉ። በእነዚያ ቀናት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎቼም ላይ፣ መንፈሴን አፈስሳለሁ። ድንቆችን በሰማያት፣ እንዲሁም በምድር፣ ደምና እሳት፣ የጢስም ዐምድ አሳያለሁ። ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ከመምጣቱ በፊት፣ ፀሓይ ወደ ጨለማ፤ ጨረቃም ወደ ደም ትለወጣለች። የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ ሁሉ፣ ይድናል፤ እግዚአብሔርም እንዳለው፣ በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም፣ መድኀኒት ይገኛል፤ ከትሩፋኑም መካከል እግዚአብሔር የጠራቸው በዚያ ይገኛሉ።
ኢዩኤል 2 ያንብቡ
ያዳምጡ ኢዩኤል 2
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኢዩኤል 2:19-32
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች